Quantcast
Channel: ኢታኖል
Viewing all 339 articles
Browse latest View live

የሪዮ ኦሊምፒክ የአትሌቲክስ ውድድር ፕሮግራም

$
0
0

በብራዚሏ ሪዮ ዲ ጄኔሮ ከተማ ባለፈው ዓርብ ሐምሌ 29 ቀን 2008 ዓ.ም. የተጀመረው 31ኛው ኦሊምያድ የአትሌቲክስ ውድድር የሚጀመረው ነሐሴ 6 ቀን ነው፡፡ የአትሌቲክስ ውድድር ፕሮግራም በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር እንዲህ ቀርቧል፡፡

ቀን

በኢትዮጵያሰዓት

ፆታ

የውድድሩዓይነት

ዙር

ተወዳዳሪዎች

06/12/08

ዓርብ

ከቀኑ 10፡10

800 ሜ

ማጣሪያ

መሀመድ አማን

ከቀኑ 11፡10

10,000 ሜ

ፍፃሜ

አልማዝ አያና፣ ገለቴ ቡርቃ፣ ጥሩነሽ ዲባባ

ከሌሊቱ 8፡30

1500 ሜ

ማጣሪያ

ገንዘቤ ዲባባ፣ ዳዊት ስዩም፣ በሱ ሳዶ

07/12/08

ቅዳሜ

ከቀኑ 10፡05

3000 ሜ መሰ

ማጣሪያ

ሶፊያ አሰፋ፣ ህይወት አያሌው፣ እቴነሽ ዲሮ

ከሌሊቱ 9፡25

10,000 ሜ

ፍፃሜ

ይግረም ደመላሽ፣ ታምራት ቶላ፣ አባዲ ሃዲስ

ከሌሊቱ 10፡05

800 ሜ

ግማሽ ፍፃሜ

መሀመድ አማን

08/12/08

እሑድ

ከቀኑ 9፡30

ማራቶን

ፍፃሜ

ትዕግስት ቱፋ፣ ማሬ ዲባባ፣ ትርፌ ፀጋዬ

ከሌሊቱ 9፡30

1500 ሜ

ግማሽ ፍፃሜ

ገንዘቤ ዲባባ፣ ዳዊት ስዩም፣ በሱ ሳዶ

09/12/08

ሰኞ

ከቀኑ 10፡25

3000 ሜ መሰ

ማጣሪያ

ታፈሰ ሰቦቃ፣ ጫላ በዩ፣ ኃ/ማርያም አማረ

ከቀኑ 11፡15

3000 ሜ መሰ

ፍፃሜ

ሶፊያ አሰፋ፣ ህይወት አያሌው፣ እቴነሽ ዲሮ

ከሌሊቱ 10፡25

800 ሜ

ፍፃሜ

መሀመድ አማን

10/12/08

ማክሰኞ

ከቀኑ 9፡30

5000 ሜ

ማጣሪያ

አልማዝ አያና፣ ሰንበሬ ተፈሪ፣ አባብል የሻነህ

ከቀኑ 10፡30

1500 ሜ

ማጣሪያ

አማን ወጤ፣ መኮንን ገ/መድህን፣ ዳዊት ወልዴ

ከሌሊቱ 10፡30

1500 ሜ

ፍፃሜ

ገንዘቤ ዲባባ፣ ዳዊት ስዩም፣ በሱ ሳዶ

 

 

 

 

Standard (Image)

‹‹ታሪክ ሲሸጥና ሲለወጥ የሚጠቃው ታሪክ ነው›› አቶ ታደለ ይድነቃቸው ተሰማ

$
0
0

ኢትዮጵያ ለአሥራ ሦስተኛ ጊዜ የተካፈለችበት የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ባለፈው ዓርብ (ሐምሌ 29 ቀን 2008 ዓ.ም.) በሪዮ ዲጄኔሮ ከተማ የተከፈተ ሲሆን፣ ለሁለት ሳምንታት እየተካሄደ ይዘልቃል፡፡ ኢትዮጵያ በ31ኛው ኦሊምፒያድ መካፈሏን ተከትሎ በብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አማካይነት በጎጆ ክሬኤቲቭ ሚዲያ የተዘጋጀው ‹‹ኦሊምፒክ - ሪዮ 2016›› መጽሔት ታትሞ ተሠራጭቷል፡፡ መጽሔቱ በይዘቱ የተፋለሰና ፈሩን የሳተ መሆኑን በመጥቀስ ሪፖርተር ባለፈው ሳምንት እትሙ ሐተታ አቅርቦበት ነበር፡፡ በብዙዎች ዘንድ በተለይም በስፖርትና ኦሊምፒክ ቤተሰብ ዘንድ አነጋጋሪ ሆኖ ስለሰነበተው መጽሔትና በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ታሪክ ዙርያ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አቶ ታደለ ይድነቃቸው ተሰማ የሚያነሷቸው ነጥቦች አሉ፡፡ አቶ ታደለ በኢትዮጵያ በዘመናዊ ስፖርትና ኦሊምፒክ አባትነት የሚጠቀሱት፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የመጀመርያ ፕሬዚዳንት፣ የኢንተርናሽናል ኮሚቴ አባል፣ የፊፋ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል፣ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ ይድነቃቸው ተሰማ (1914-1979) ልጅ ናቸው፡፡ አቶ ይድነቃቸው አፍሪካና ደቡብ አሜሪካ በፊፋ ውስጥ የነበረውን የአውሮፓ ፍጹም የበላይነት ለመታገል የመጨረሻ ስምምነት ለማድረግ ከ43 ዓመት በፊት በሪዮ ዲጄኔሮ በተዘጋጀው ስብሰባ ላይ አቶ ታደለ የመካፈል ዕድል አግኝተው ነበር፡፡ የኢትዮጵያን የስፖርት ታሪክ ከኦሊምፒክና ከፊፋ ጋር የተያያዙ ዋና ዋና ጉዳዮች፣ እንዲሁም የአቶ ይድነቃቸው ተሰማ ታሪክን አደራጅተው አሳትመዋል፡፡ በኦሊምፒክ መጽሔት ይዘት፣ በኢትዮጵያ ስፖርትና ኦሊምፒክ ጥንተ ታሪክ ዙርያ አቶ ታደለ ይድነቃቸው ተሰማን ሔኖክ ያሬድአነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ‹‹ኦሊምፒክ - ሪዮ 2016›› የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ መጽሔትን እንዴት አገኙት?

አቶ ታደለ፡- ሁለት ነገር ነው የታዘብኩት፤ ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ መሳተፍ የጀመረችበት 60ኛው ዓመትና የሪዮ ኦሊምፒክ መጽሔት መደባለቅ፡፡

የኦሊምፒክ መጽሔት የአንድ ብሔራዊ ኦሊምፒክ መጽሔት ብቻ አይደለም፡፡ ስታንዳርድ የሆነ እያንዳንዱ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በያንዳንዱ ተሳትፎ የኦሊምፒክ ፍልስፍናዎች የሚያከብርና የተቀበለ መሆኑን የሚያውጅበት፣ የዘመናዊ ኦሊምፒክ መሥራቹን ባሮን ደኩበርቲን ስሙን የሚጠቅስበት፣ ከዚያ በኋላ የራሱን ብሔራዊ ኦሊምፒክ የሚያስተዋውቅበት፣ ከአገሪቱ ስፖርት መሪዎች፣ ከብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴና ከአገሪቱ መሪ መልዕክት የሚተላለፍበት ነው፡፡ እንዲሁም ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች አገሪቱ ካሁን በፊት ያደረገቻቸው የኦሊምፒክ ውድድር ታሪኮች፣ ኢትዮጵያዊ ሆነው የኢንተርናሽናል ኦሊምፒክ ኮሚቴ ውስጥ ያገለገሉና አባል የነበሩ ሰዎች የሚታወሱበት ከሌሎች ጋርም ልውውጥ የሚደረግበት ነው፡፡

እንደ ነጋዴ የንግድ ካርዱን ኮክቴል ላይ እንደሚለዋወጠው፣ ስለየ አገሩ በጥቂቱ ለማወቅ፤ እያንዳንዱ አገር የኦሊምፒክ መጽሔቱን ይለዋወጣል፡፡ ለኦሊምፒክ ጨዋታዎች የሚዘጋጀው መጽሔት በማንኛውም መልኩ መደበኛ የታሪክ መጽሐፍ ሊሆን አይችልም፡፡ ኢንፎርሜሽን የሚሰጥበት ነው፡፡ 60ኛ ዓመት፣ 50ኛ ዓመት፣ 25ኛ ዓመት የተለዩ ነገሮች ናቸው፡፡ በነዚህ ጊዜ ከኋላ ከመነሻው ጀምሮ የነበሩ ክንውኖች፣ ሰዎችም የሚታወሱበት፣ ከየት ተነሣን? የት ደረስን? የሚቃኝበት ነው፡፡ ሁለቱ በመቀላቀላቸው የመጀመርያው ስህተት ተሠርቷል፡፡ የኢትዮጵያን የ60 ዓመት ኦሊምፒክ ታሪክ ከኢትዮጵያ የሪዮ ኦሊምፒክ መተዋወቂያ ሰነድ ጋር አትቀላቅለውም፤ እንደ መነሻ ትጠቅሰዋለህ እንጂ፡፡

ሪፖርተር፡- አጻጻፉንስ እንዴት አዩት?

አቶ ታደለ፡-  ታሪክን በዘፈቀደ የመጻፍ ነገር ብሔራዊ ውይይት የሚያስፈልገው ነው፡፡ በአገራችን በሁሉም ሴክተር (ዘርፍ) እየተለመደ የመጣ መጥፎ ባህል አለ፡፡ የዛሬውንና ያለፈውን ትውልድ ያለያየ፣ እንዳይተዋወቁ ያደረገ ነው፡፡ በመጽሔቱ ውስጥ የተፈጠሩት ስህተቶች በሪፖርተር ከነዕርማታቸው ተጠቁሟል፡፡ ነገር ግን ከዚህ ከኦሊምፒክ ጋር በተያያዘ ውሸቱ እንዴት ተለመደ? ወደ ሚለው ብንሄድና የተወሰኑ ነገሮች ባነሳ አስፈላጊ ነጥቦች ናቸው፡፡ አንደኛ ታሪክ የሚለወጥበት ምክንያት ምንድን ነው? የሚለወጥበት ምክንያት የአንድ ሰው ታሪክ ለመለወጥ ይሆናል፡፡ በዘመኑ ሁሉም ኢትዮጵያውያን በምሥረታው ጊዜ የነበሩት የሚያውቁት የዘመናዊ ስፖርት መሥራች፣ ዛሬ እሱ አይደለም የሚል ታሪክ ለመፍጠር ሊሆን ይችላል፡፡ እንዳየሁትም ዓላማው ያ ነው፡፡ ለአቴንስ (1996 ዓ.ም.) እና ለአትላንታ (1988 ዓ.ም.) የተዘጋጁትን የኦሊምፒክ መጽሔቶች አግኝቼ በጣም ገርሞኝ ነበር፡፡ ኢንተርናሽናል ኦሊምፒክ ኮሚቴ በስፖርት የዘር አድልዎን የታገለና የከለከለ ድርጅት ነው፡፡ በዘር አድልዎ አያምንም የሚል ነገር አለው፡፡ ኢንተርናሽናል ኦሊምፒክ ኮሚቴ የዘር አድልዎ እየተገበረ፣ መተግበር አትችልም ብላ በቦይኮት ያስቆመች ኢትዮጵያ መሆኗ እየታወቀ፤ ኢንተርናሽናል ኦሊምፒክ ኮሚቴ ዘረኝነትን አትቀበሉ ብሎ ኢትዮጵያን ያስተማረ ይመስል፣ እንዲህ ያለ ነገር መጽሔት ላይ ጽፎ መሄድ ተገቢ ነው ወይ? ነፍሱን ይማርና ለብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት አቶ አሰፋ ማሞ ጠይቄ ነበር፡፡ አስገራሚ መልስ ነበር የሰጠው፡፡ ትክክል ነው፤ ይኼ ታሪክ የኢትዮጵያ መሆኑን እናውቃለን፣ ግን የማሳተሚያው ፈንድ የሚመጣው ከኦሊምፒክ ሶሊዳሪቲ ስለሆነ ብዙ ጊዜ እነሱ የፈለጉትን የመጻፍ ሁኔታ ውስጥ ትገባለህ፤ ይኼ ግን ይታረማል ብሎ ነበር፡፡ ያ ወቅት ኢንተርናሽናል ኦሊምፒክ ኮሚቴ የገንዘብ ኃይሉን ተጠቅሞ የአገሮችን የኦሊምፒክ መጽሔት ስፖንሰር እያደረገ እርሱን እንዲያወድሱት የሚያጽፍበት ወቅት ነበር፡፡ አንዱ የታሪክ ለውጥ በዚያ ዘመን ነበር፡፡ ሁለተኛው የታሪክ ለውጥ በግምት ላይ የተመሠረተውና የአንድን ግለሰብ ታሪክ ከመለወጥ ጋር የተያያዘው አጠቃላይ የአገሪቱን ስፖርት ታሪክ የመለወጥ አዝማሚያ ነው፡፡ እዚያ ላይ ተጠቂ የሚሆነው በአንደኛ ደረጃ ታሪክ ነው፡፡ ታሪክ ሲሸጥና ሲለወጥ የሚጠቃው ታሪክ ነው፡፡ ሦስተኛ በነዚያ ዓመታት የአገሪቱን ስፖርት የሚያገለግሉት ሰዎች በሙሉ ነፃ አገልጋዮች ናቸው፡፡ ትርፍ ጊዜያቸውን የመኪና ነዳጃቸውን አንዳንዴም ገንዘባቸውን ሁሉ ለአንዳንድ ሥራዎች እያወጡ የኖሩ ሰዎች ናቸው፡፡ የነሱ ታሪክ ነው እየተለወጠ ያለው፡፡

ሪፖርተር፡- የብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ታሪክ ተለውጧል ሲሉ ምን ማለትዎ ነው?

አቶ ታደለ፡- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ታሪክ አመሠራረት እንዳለ ተለውጧል፡፡ ኦሊምፒክ ኮሚቴው እ.ኤ.አ. በ1954 (1946 ዓ.ም.) ተመሠረተ የሚል ወጣ፡፡ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በ1954 አልተመሠረተም፡፡ ታሪኩ ሌላ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ስፖርት ኮንፌዴሬሽን ተብሎ በመንግሥት ማስታወቂያ የተቋቋመ ከፊል መንግሥታዊ ከፊል ሕዝባዊ የሆነ ተቋም ለጊዜው በተሾመለት ዋና ጸሐፊ ኤድዋርድ ቪርቪሊስ በሚባል ግሪካዊ አማካይነት፣ በ1954 አቴንስ ላይ ለነበረው የኢንተርናሽናል ኦሊምፒክ ኮሚቴ ጉባኤ ቃል ገብቶ፣ ወደፊት አምስት ፌዴሬሽኖችና ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴውን እናቋቁማለን፤ እስከዚያው ስፖርት ኮንፌዴሬሽኑ ያንን ሠርቶ እስኪጨርስ ኮንፌዴሬሽኑ የብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የሽግግር ወኪል ሆኖ እንድንካፈል ይፈቀድልን ብሎ ተፈቅዶ የገባንበት እንጂ፣ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የተቋቋመበት ጊዜ አይደለም፡፡

የተዘረዘሩት እነዚያ ስፖርቶች ወደ ፌዴሬሽን ተቃርበው የነበሩት የኢትዮጵያ ስፖርት ጽሕፈት ቤት በ1936 ዓ.ም. ሲቋቋም እግር ኳስ፣ ብስክሌትና ቦክስ ነበሩ፡፡ ትራክ ኤንድ ፊልድ (አትሌቲክስ) የሚባለው የሜዳ ሩጫ በኋላ ላይ የስዊድን የጦር አሠልጣኞች ሲመጡ በወታደራዊ ክፍሎች ውስጥ ነው የጀመሩት፡፡ ለዚህም ነው አንድም ጊዜ ከትምህርት ቤቶች ወይም ከሌላ አካባቢ አገሪቱን የወከለ አትሌት ወጥቶ የማያውቀው፡፡ ያ ዘመን ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የተቋቋመበት ዘመን አይደለም፡፡ ወደፊት እናቋቁማለን በሚል ቃልኪዳን የመካፈል ዕድል የተገኘበት ዘመን ነው፡፡ ስህተቱ የሚጀምረው እዚህ ጋ ነው፡፡  ከርሱ ጋር በተያያዘ በደብዳቤ የተደረጉትን ልውውጦች በቁንፅል እየተመለከቱ ብስክሌትና አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከእግር ኳስ ቀድመው ተቋቁመው ነበር የሚሉ አሉ፡፡

እዚህ ላይ የሚነሳ ጥያቄ አለ፡፡ ብስክሌትና አትሌቲክስ ከእግር ኳስ በፊት ተቋቁመዋል ሲባል የት ነበረ ውድድሩ? ውድድር በሌለበት ፌዴሬሽን ከየት ይመጣል? ፌዴሬሽን አወዳዳሪ አካል ነው? አወዳዳሪ አካላቱስ እነማን ነበሩ? ከ1941 ዓ.ም. ጀምሮ አወዳዳሪዎች የነበሩት እነማን ነበሩ? ተወዳዳሪዎችስ? መልስ የለም፡፡ ብስክሌት በጣሊያን ወረራ ጊዜ ነበር፡፡ ጣሊያኖች በአሁኑ ጊዜ ተወዳጅ የሆነው ቱር ደፍራንስን ሁለት ጊዜ አሸንፈው ነበር፡፡ የጣሊያን ብሔራዊ ስሜት የሚንፀባረቅበት ስፖርት ነበርና በቅኝ ግዛት በያዘቻቸው አገሮች ሁሉ ብስክሌት አስገብታ ያገር ተወላጅ ጥቁሩ ተለያይቶ ይጫወት ነበር፡፡ እኛም አገር በዚያን ጊዜ ተስፋፍቷል፡፡ ያ በፌዴሬሽን ሳይሆን በአገር ተወላጆች ስፖርት ጽሕፈት ቤት በሚባለው ውስጥ ነው፡፡ ካሳ ፈዲል ታዋቂ የነበረበት ያ ዘመን ነው፡፡ ‹‹ገኖ ይጠራል ስማቸው በኮርስ ካሳ በኳስ ይድነቃቸው›› ተብሏል፡፡ ያ ዘመን ካሳ ፈዲልና ሌሎችም አሁን ስማቸውን የማላስታውሳቸው ብዙ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ብስክሌት መወዳደር የጀመሩበት ዘመን ነው፡፡ ያንን የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን ብሎ መመዝገብ አይቻልም፡፡ የቅኝ ግዛት ተቋም ነው፡፡ የአገር ተወላጆች የስፖርት ጽሕፈት ቤት እንጂ ፌዴሬሽን አልነበረም፡፡

ከዚያ በኋላ አባቴ [ይድነቃቸው ተሰማ] እንደሚያስታውሰው፣ ስፖርት ጽሕፈት ቤት የሚለውን ሲያቋቁም የርሱ እምነት እነዚያ በጣሊያን ጊዜ ብስክሌትና ቦክስ ለተጫወቱ ሁሉ ውድድር እናዘጋጃለን የሚል ምኞት ነበረው፡፡ ነገር ግን እነ ካሳ ብስክሌቶቻቸው አርጅተዋል፡፡ ለቦክሰኞቹም ጓንት አልነበረም፡፡ ስለዚህ እግር ኳሱ ብቻ ቀጠለ፡፡ ብስክሌትና ቦክስ ከ1936 እስከ 1941 ዓ.ም. በነበረው ጊዜ በስፖርት ጽሕፈት ቤት ሥር ውድድር አልተደረገላቸውም፡፡ በ1941 ዓ.ም. ላይ የኢትዮጵያ ስፖርት ጽሕፈት ቤት ወደ ኢትዮጵያ ፉትቦል ፌዴሬሽን ይለወጥ ሲባል ብስክሌትና ቦክስ በዚያው ተረሱ፡፡ ደግሞም ሁለቱን ማካሄድ እንደ እግር ኳስ በገንዘብ ቀላል አይደለም፡፡

እግር ኳስ ዝም ብለህ ሜዳ ትሰጠዋለህ፤ ቤተሰብ ትጥቅ አቡጀዲ ገዝቶለት ነው የሚወዳደረው፣ ቀላል ነው፣ ብዙ ወጪ የለውም፡፡ ጓንትና ብስክሌት መግዛት ውድ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ፉትቦል ፌዴሬሽን መልኩን ነው የለወጠው፡፡ መጀመርያ በስፖርት ጽሕፈት ቤት ውስጥ መቋቋሙ ተመዝግቦለታል፡፡ ነገር ግን ፊፋ በሚፈልገው መልኩ ነፃ ሆኖ የተቋቋመበት ዘመን 1941 ዓ.ም.፣ እነ ሜጄር ጄኔራል ሙሉጌታ ቡሊ (በዚያን ጊዜ የክብር ዘበኛ ዋና አዛዥ የነበሩ)፣ ሌተና ኮሎኔል ከበደ  ገብሬ (በኋላ ሌተና ጄኔራል)፣ ሌተና ኮሎኔል ኃይሌ ባይከዳኝ፣ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረጉበት ዘመን ነበር፡፡ አቶ ገብረሥላሴ ኦዳ (ከቅዱስ ጊዮርጊስ) እንዲሁ፡፡ እያንዳንዱ ክለብ በሥራ አስፈጻሚ ውስጥ እንዲገባ ተደርጎ የመቻል (የምድር ጦር) ተወካይ ሌተና ኮሎኔል ከበደ ገብሬ ፕሬዚዳንት፣ የጊዮርጊስ ተወካይ ከነበሩት ውስጥ ይድነቃቸው ተሰማ ዋና ጸሐፊ እንዲሆን ተደርጎ የተቋቋመበት ጊዜ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ግሪካዊው ቬርቪሊስ ከኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ታሪክ ጋር ተያይዞ ሲነሳ ይሰማል፡፡

አቶ ታደለ፡- ይኼ ኤድዋርድ ቬርቪሊስ የሚባለው ሰው ዛሬ እንደሚተርከው ለኦሊምፒክ ተሳትፎ ሲባል ከሌላ ቦታ የመጣ ሰው አይደለም፡፡ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ውስጥ በነበረው የስፖርት ጽሕፈት ቤት ውስጥ በአማተር አገልጋይነት የቴክኒክ አማካሪ ሆኖ ይሠራ የነበረ፣  ከአምስት ዓመታት በኋላ ጃንሜዳ በተደረገው ስብሰባ በኋላ የነ አበበ ቢቂላ አሠልጣኝ በነበረው በኦኒ ኒስካነን በድምፅ ተበልጦ ሳይገባ የቀረ፣ በዚያም አኩርፎ የወጣ ነው፡፡

ከዚያ በኋላ የስፖርት ኮንፌዴሬሽን እንዲቋቋም ለንጉሠ ነገሥቱ ካመለከቱት የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር አብሮ የቀረበና በዚያ ምክንያት ዋና ጸሐፊ የሆነ እንጂ ቀደም ሲል ኢትዮጵያ ውስጥ በስፖርት የማይታወቅ ሰው ሆኖ አይደለም፡፡ አሌክሳንደሪያ ውስጥ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ የአካል ማጎልመሻ አስተማሪ ነበር፡፡ ከዚያ ኢትዮጵያ መጥቶ ቡና ነጋዴ ሆኖ ሳለ በ1936 ዓ.ም. በተቋቋመው የስፖርት ጽሕፈት ቤት ውስጥ ረዳት የቴክኒክ አማካሪ ሆኖ ገባ፡፡ ከአምስት ዓመት በኋላ ፉትቦል ፌዴሬሽኑ ራሱን ሲችል የክብር ዘበኛ ተወካይ ኦኒ ኒስካነን ከሱ የተሻለ ድምፅ አገኘና ተመረጠ፡፡ አኩርፎ የወጣ እንጂ አዲስ ለስፖርቱ ተብሎ ከግሪክ የመጣ ሰው አይደለም፡፡ ዛሬ እንደሚባለው አይደለም፡፡ የውሸት ታሪክ ነው የሚጻፈው፡፡

የብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ መነሻ ታሪክ ሰፊ ነው፡፡ ኮንፌዴሬሽኑን በተመለከተ በዚያን ጊዜ የነበሩ ከፍተኛ ባለሥልጣኖች ሜጀር ጄኔራል መርዕድ መንገሻ (በኋላ ሌተና ጄኔራል) ሌተና ኮሎኔል ታምራት ይገዙ ባንድ በኩል፣ ሌተና ጄኔራል አቢይ አበበ በሌላ በኩል ሆነው ብዙ የተሟገቱበት በኋላ እየተለወጠ የመጣ አደረጃጀት ነው፡፡ የስፖርት ኮንፌዴሬሽን አመሠራረት ራሱን የቻለ ታሪክ ስለሚፈልግ እዚህ ላይ ባንገባበት ጥሩ ነው፡፡ ባጠቃላይ ያ የስፖርት ኮንፌዴሬሽን እንጂ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አይደለም፤ አልነበረም፡፡

ሪፖርተር፡- አትሌቲክስ ፌዴሬሸን መቼ ተቋቋመ?

አቶ ታደለ፡- አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከፉትቦል በፊት ተቋቋመ ማለት ብቻ ሳይሆን፣ ሌተና ኮሎኔል ጌታሁን ተክለማርያም የመጀመርያው ፕሬዚዳንት ነበሩ የሚል የፈጠራ ታሪክ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴውም ሆነ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ ዛሬም ድረስ ድረ ገጹ ላይ ለጥፏል፡፡ በጣም አሳፋሪ ነው፡፡

አንደኛ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የተቋቋመው በየካቲት 1953 ዓ.ም. ሲሆን፣ እግር ኳስ በ1936 ዓ.ም. ነው የተቋቋመው፤ ልዩነቱ ሩቅ ነው፡፡ ሁለተኛ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን መሥራች አባላት ስም ዝርዝር አለ፡፡ ሌተና ኮሎኔል ብርሃነ ተፈራ (የፖሊስ ሠራዊት አባል) የመጀመርያው ፕሬዚዳንት ሆነው እስከ 1958 ዓ.ም. አገልግለዋል፡፡ አቶ ልዑልሰገድ በቀለ፣ ተቋመ ወልደጻድቅ፣ ብርሃነ ዳሬሳ፣ ለገሠ በየነ፣ ዑስማን መሐመድ፣ ሻምበል ገበየሁ ዱቤ፣ ጥግነህ አስፋው፣ ወልደብርሃን ተስፋማርያም፣ ዝግጁ በልሁ፣ እሸቴ ህለተ ወርቅና መቶ አለቃ ተፈሪ በንቲ (ምናልባትም በኋላ ብርጋዲየር ጄኔራል ሆነው አገሪቱን የመሩት ናቸው) መሥራቹ ትውልድ ይሄ ነው፡፡ ጌታሁን ወይም ጌታነህ ተክለማርያም ማለት የነ ሻምበል ዘላለም ደስታ እኩያ ናቸው፡፡ የነ ሻምበል ዘላለም አለቃ የነበሩ ናቸው፡፡ በደርግ የመጀመርያ ዓመታት የተደረጉትን የጦር ኃይሎች ውድድር አዘጋጅ ኮሚቴ ሊቀመንበር የነበሩ በጣም ወጣት ናቸው፡፡ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሲመሠረት በዚያ ቦታ የሉም፡፡ ተፈሪ በንቲ ሊቀመንበር ባልነበሩበት ፌዴሬሽን ውስጥ ሊቀመንበር ነበረ ብሎ ማቅረብ በታሪክ ላይ የተሠራ ግፍ ነው፣ ትክክል አይደለም፡፡

እንደዚህ ዓይነቶቹ ነገሮች የሌሎችንም ታሪኮች እየደበቁ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ስፖርት ውስጥ እንዳልኩህ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ባለሥልጣኖች መካከል ኢትዮጵያ ውስጥ በስፖርት ያላገለገለውን መቁጠር ይቀላል፡፡ አብዛኞቹ ነፃ አገልግሎት በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ሰጥተዋል፡፡ የነርሱንም ስም የመሠረዝ ነው፡፡ ከባለሥልጣኖቹ ውጪ የነጋዴው ኅብረተሰብ በጣም ብዙ አለ፡፡ የነርሱን ሁሉ ታሪክ መሠረዝ ነው፡፡ ለምን እንዲህ ማድረግ እንደተፈለገ ያነሣሁት ነጥብ አለ፡፡ ዓላማው ያ ቢሆንም ጉዳቱ ግን በዚያ ላይ ብቻ አይቆምም፡፡ 

ሪፖርተር፡- ኮንፌዴሬሽን በተመለከተ በነጋሪት ጋዜጣ 1941 ዓ.ም. የወጣው እንዴት ይታያል?

አቶ ታደለ፡- ስለ ኢትዮጵያ የስፖርት ኮንፌዴሬሽን መቋቋም የወጣ የመንግሥት ማስታወቂያ ነው፤ ያኔ ፉትቦሉ በፊፋ ተመዝግቦ ነበር፡፡ ሌሎቹስ ወዴት ነው የሚመዘገቡት? ከፉትቦል ሌላ፣ ሌላ ፌዴሬሽን የለም፡፡ ኮንፌዴሬሽኑ ሌሎቹን ካቋቋመ በኋላ ዓላማው ምንድን ነው? ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በዚያን ጊዜ ለማቋቋም የተቸገረው፣ ንጉሠ ነገሥቱም ወዲያውኑ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ይቋቋም ያላሉት፣ ለማቋቋም የሚያስፈልጉ አምስት ፌዴሬሽኖች ስላልነበሩ ነው፡፡ ዛሬ አምስት ፌዴሬሽኖች ነበሯት እየተባለ ነው፡፡ የዛሬው ታሪክ እንደዚያ ነው የሚለው፡፡ እነ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ቀድመው ከተቋቋሙ፣ ኮሚቴው ነበረ ማለት ነው፡፡ ያን  ጊዜ ይኼን ያሉት ኮ ፌዴሬሽኖችን ቀድሞ የማደራጀት አስፈላጊነቱን ስለተረዱ ነው፡፡ መሠረታዊ በመሆኑ በሕዝብ ማስታወቂያ ላይ ተጠቅሷል፡፡ ያም ባይኖር ኢንተርናሽናል ኦሊምፒክ ኮሚቴ አይቀበልም፡፡ ኮሚቴው የሚመዘግብህ በኦሊምፒክ የታወቁ የአምስት ስፖርቶች ፌዴሬሽኖች ሲኖሩ ነው፡፡

      በ1941 ዓ.ም. የመንግሥት ማስታወቂያ ቢወጣም ለ19 ዓመታት ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ማቋቋም አልተቻለም፣ ምክንያት አለ፡፡ ፌዴሬሽን መመሥረት ቀላል ነገር አይደለም፡፡ የቅርጫት ኳስ ውድድር አዘጋጅተህ ተሳታፊ ላታገኝ ትችላለህ፡፡ ተወዳጅነትም ላያገኝ ይችላል፡፡ የማስተማር፣ ተመልካች የመሳብ ነገር አለ፡፡ ጊዜ ይወስዳል፡፡ ሒደት ነው፡፡ በ1960 ዓ.ም.ም ቢሆን ኦሊምፒክ ኮሚቴን ያቋቋምነው ተሳክቶልን አምስቱ ተሟልተው ሳይሆን፣ ከኢንተርናሽናል ኦሊምፒክ ኮሚቴ ጋር በአፓርታይድ ምክንያት የተቀያየምን ስለሆነ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የላችሁም ብሎ እንዳያባርረን በጥድፊያ የተደረገ ነው፡፡ ስታዲየሙ ውስጥ ያሉት ቢሮዎች በሙሉ ስም ተጽፎባቸው ፌዴሬሽኖቹ ተቋቁመዋል ተብሎና ማመልከቻ ቀርቦ፣ የአባልነት ክፍያም ተከፍሎ ኢንተርናሽናል ኦሊምፒክ ኮሚቴ ሳይወድ በግዱ ኢትዮጵያ ከአምስት በላይ ፌዴሬሽኖች አላት ብሎ የተቀበለን በ1960 ዓ.ም. ነበር፡፡ የሕዝብ ክፍል ማስታወቂያ እዚህ ላይ ተንፀባርቋል፡፡ ነገር ግን እርሱ ኖረ አልኖረ ኢንተርናሽናል ኦሊምፒክ ኮሚቴ ለመመዝገብ ግዴታ ነበር፡፡ በ1960 ዓ.ም. ስንመዘገብ እውነቱን እንነጋገር ከተባለ አምስት የሚንቀሳቀሱ ፌዴሬሽኖች ነበሩን? አልነበሩንም፡፡

ዛሬስ? ካሳዛነኝ ነገር አንዱ ከ60 ዓመት መካፈል በኋላ ዛሬ የምንካፈለው በ38 አትሌቶች ነው፡፡ ሁለተኛ የምንካፈልባቸው ስፖርቶች ከማደግ ይልቅ ወደ መውረድ ማዘንበላቸው፡፡ ሦስተኛ ዛሬ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ በሚውልበት ጊዜ አንድ ብስክሌተኛ ብቻ ማካፈል በጣም አሳፋሪ ነው፡፡ ለሮም ኦሊምፒክ በዚያን ጊዜ የብስክሌት ፌዴሬሽን አልነበረም፡፡ አንድ ግሪክ ነው (ጋሽ ገረመው ደንቦባን ልትጠይቀው ትችላለህ) በ7 ሺሕ ብር ብስክሌት የገዛላቸው፡፡ መንግሥት በጀት ሲለቅ ነው ለግሪኩ የተከፈለው፡፡ ያን ጊዜ ግን ሦስት ተወዳዳሪዎች ነበሩ፡፡ ዛሬ አንድ ለምን? በቶኪዮም በሜክሲኮም በርካታ ነበሩ፡፡ ዞሮ ዞሮ ዕድገት የለም፤ የተለወጠ ነገር የለም፡፡ በስፖርቱም ዓይነት ሆነ በስፖርተኞች ቁጥር የሜዳሊያ ቁጥራችን የጨመረው በዚያን ጊዜ የሌሉ የሴቶች የማራቶን፣ 10ሺ፣ 5ሺ፣ 1,500፣ 3,000 መሠናክል ዛሬ ስለተጀመሩ ነው እንጂ አይጨምርም ነበር፡፡ እኛና ኬንያ በመካከለኛ ርቀትና በማራቶን ጥሩ ውጤት አለን፡፡ ያ በሴቶችም ሲሆን ዕጥፍ ሆነ እንጂ አንድም ዕድገት የለም፡፡ መሸፋፈን አያስፈልግም፡፡ 60 ዓመታት ሙሉ አንድ ቦታ ለምን ቆምን ብሎ በአልማዝ ኢዮቤልዩ አጋጣሚ መነጋገር ይገባ ነበር፡፡ የዛሬ 60 ዓመት ከነበርንበት ቦታ ላይ ለምን ቆምን? ያኔ ገንዘብ የለም፣ ባለሙያ የለም፡፡ በዚያ ሁሉ መወዳደር ከቻልን ዛሬ ከ60 ዓመት በኋላ በዚህ ሁሉ ሚሊዮን ብር ለምን ቆምን? ይኼ ነው መታየት ያለበት፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን መጽሔቶች ላይ የምናየው ስህተት እንዴት ነው ማረም የሚቻለው? ለተፈጠሩት ስህተቶችስ ይቅርታ የሚጠይቅ አካል አይኖርም?

አቶ ታደለ፡- እኔ በዚህ ጉዳይ ላይ ከወ/ሮ ዳግማዊት ግርማይ ጋር አንድ ጊዜ ተወያይቼያለሁ፡፡ የብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴያችን ታሪክ መለወጥ ተገቢ እንዳልሆነ፡፡ በዚያን ጊዜ የቤጂንግ ኦሊምፒክ (2000 ዓ.ም.) ተቃርቦ ስለነበረ፣ ሩጫ ላይ ስለነበሩ ግዴለም እንደመጣሁ አጣርቼ መልስ እሰጣለሁ ብለው በዚያው ሁኔታዎች ቀሩ፡፡ ዛሬም ታሪኩ ላይ መሰባሰብ ያስፈልጋል፡፡ ሰነዶቹ እዚያው አሉ፡፡ የጠፋው አንብቦ እውነተኛውን የሚዘግብ ነው፡፡ የበረከተው ደግሞ የእውነቶቹን ሸፍኖ አዳዲስ የፈጠራ ታሪክ የሚያጎላው ነው፡፡ አንድ ያየሁት አሳዛኝ ነገር፣ በዚህ ባነሳኸው ነጥብ ላይ ይቅርታ የመጠየቅ ባህል የለንም፡፡ ስህተታቸውን እያወቁ ይቅርታ የመጠየቅ ባህሉ የለም፡፡ ይኼን ነገር በብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው አይቻለሁ፣ በጣም ነው የገረመኝ፡፡  

      አንድ ጊዜ የብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ 50ኛ ዓመት ሲከበር ለይድነቃቸው ተሰማ ሽልማት ተቀበል ብለው በቃል ጋበዙኝ፡፡ ትክክል አለመሆናቸው ነገርኳቸው፡፡ ማንኛውም ሽልማት ሲሰጥ መጀመርያ የሚሸለመው ምን ሠራ ተብሎ ነው? በናንተ ድረ ገጽ ብቁ ስላልነበረ ግሪክ መጥቶ ተሹሟል ነው ያላችሁት፡፡ ብቁ ያልነበረ ሰው ለምን ትሸልማላችሁ? ስለዚህ አብራሩልኝ ብዬ ብጠይቅ መልስ አልመጣም፡፡ ቢሆንም ባይሆንም ተገኝልን አሉ፤ አልገኝም፣ ቤተሰቡም አይቀበልም አልኩ፡፡ ግን በግድ እነሱ ሰጪ፣ እነሱ ተቀባይ ሆኑ፡፡ ማን እጅ ላይ እንዳለ አላውቅም፡፡ እዚያው ተቀባበሉት፡፡ ይቅርታ የጠየቀ ሰው የለም፣ ይቅርታ የመጠየቅ ባህል የለም፣ በጣም አሳፋሪ ነው፡፡ ስህተት መሥራት አንድ ራሱን የቻለ ችግር ሆኖ፤ ስህተቱ ተነግሮ ይቅርታ አለመጠየቅ በማንኛውም መሥፈርት ትልቅ ስህተት ነው፡፡ ደግሞስ ታሪክህን ራስህ ታዘጋጃለህ እንጂ እንዴት ለውጭ አሳልፈህ (አውት ሶርስ አድርገህ) ትሰጣለህ? ይኸው ነው የሚሰማኝ፡፡

 

     

 

 

Standard (Image)

ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ከግብፅ በድል ተመለሰ

$
0
0

ማዳጋስካር በ2009 ዓ.ም. ለምታዘጋጀው የከ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ቀይ ቀበሮዎቹ) የግብፅ አቻውን 3ለ1 በመርታት በድል ተመልሷል፡፡ ቅዳሜ ሐምሌ 30 ቀን 2008 ዓ.ም. ካይሮ ላይ ጨዋታውን ያደረገው ብሔራዊ ቡድኑ በመጀመሪያ 20 ደቂቃዎች ጎል ቢቆጠርበትም፣ የመጀመሪያ አጋማሽ ከመጠናቀቁ ቀደም ብሎ ግብ አስቆጥሮ ጨዋታውን መቆጣጠር ችሏል፡፡

በተለይ ባለሜዳዎቹ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች የተሻለ ሙከራ በማድረግ ከፍተኛ ብልጫ ያሳዩ ቢሆንም፣ ቀይ ቀበሮዎቹ በጥንቃቄ መጫወታቸው ከዚህ ቀደም የሰሜን አፍሪካ አገሮች በኢትዮጵያ ላይ የሚያሳዩትን የበላይነት በከፊሉም ቢሆን ማስቀረት እንደቻሉ ተነግሮላቸዋል፡፡ በጨዋታውም 17ኛው ደቂቃ ላይ የግብፅ ብሔራዊ ቡድን በሞሐመድ አብዱላህ ግብ ቀዳሚ መሆን ቢችልም፣ በ24ኛው ደቂቃ የግብ ጠባቂን ስህተት በመጠቀም ለቀበሮዎቹ ጫላ ተሺታ የመጀመሪያ ግብ ማስቆጠር ችሏል፡፡

ቀሪዎችን ሁለት ግቦች አቡበከር ናስርና ሚኪያስ መኮንን ማስቆጠር ችለዋል፡፡ ለ27 ቀናት በሐዋሳ ዝግጅት ሲያደርግ የሰነበተው ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን የመልስ ጨዋታውን ከሁለት ሳምንት በኋላ በድሬዳዋ ከተማ እንደሚያደርግ ቢገለጽም ዋና አሠልጣኙ አጥናፉ ዓለሙ ልምምድ በሚያደርጉበት ሐዋሳ ቢደረግ የተሻለ እንደሆነ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

የቀድሞ የኤሌክትሪክና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አሠልጣኝ የነበሩት የብሔራዊ አጥናፉ ዓለሙ ታዳጊዎቹ ያላቸውን ፍላጎት አድንቀዋል፡፡ እንደ ዋና አሠልጣኙ ገለፃ ከሆነ የመልስ ጨዋታ ቦታ በተመለከተ ‹‹ጨዋታ ከማድረጋችን በፊት ቢገለጽልን ቀድመን ልምምዳችን በድሬዳዋ እናደርግ ነበር፤›› በማለት አስተያየታቸውን ለሪፖርተር አብራርተዋል፡፡

በ1997 ዓ.ም. ቦትስዋና ላይ በተደረገው የአፍሪካ ታዳጊዎች ሻምፒዮና ላይ ግብፅ ኢትዮጵያን 1-0 በማሸነፍ ሦስተኛ በመሆን ውድድሩ ማጠናቀቁ ይታወሳል፡፡

እ.ኤ.አ. በ1995 የጀመረው የአፍሪካ ዋንጫን ጋና፣ ናይጄሪያና ጋምቢያ ሁለት ሁለት ጊዜ ዋንጫ በማንሳት በቀዳሚነት ተቀምጠዋል፡፡ አምና ማሊ ማሸነፏ ይታወሳል፡፡

Standard (Image)

የሴቶችና የወንዶች 10,000 ሜትር ዓርብና ቅዳሜ ይካሄዳል

$
0
0

-  የአባዲ ሐዲስ ዕድሜ እያነጋገረ ነው

በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው 31ኛው ኦሊምፒያድ ከተጀመረ ስድስተኛ ቀን አስቆጥሯል፡፡ ከተለያዩ የዓለም አገሮች የተሰባሰቡት ስፖርተኞች በተገኙበት የዘንድሮው የሪዮ ኦሊምፒክ ጨዋታ ሐምሌ 29 ቀን 2008 ዓ.ም. በድምቀት ሲከፈት፣ የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በዋናተኛው አቤል ኪሮስ መሪነት ወደ ስታዲየም ሲገባ አቀባበል ተደርጎለታል፡፡

ኢትዮጵያ በወርቃማ ውጤቷ የምትታወቅበት የረዥም ርቀት ሩጫ ከነገ በስቲያ ዓርብ ነሐሴ 6 ቀን በሚካሄደው የሴቶች 10,000 ሜትር ፍጻሜ ውድድር የሚጀመር ሲሆን፣ አዲሷ ኮከብ አልማዝ አያና፣ ገለቴ ቡርቃ እና የሁለት ኦሊምፒኮች ባለድሏ ጥሩነሽ ዲባባ የአገሪቱን ድል እንደሚያስቀጥሉ ይጠበቃል፡፡ በመካከለኛ ርቀት በ800 ሜትር መሐመድ አማን፣ በ1,500 ሜትር ገንዘቤ ዲባባ፣ ዳዊት ሥዩምና በሱ ሳዶ የመጀመርያ ማጣሪያ ውድድራቸውንም ያከናውናሉ፡፡

ቅዳሜ በሚካሄደው የ10,000 ሜትር ወንዶች ፍጻሜም ይገረም ደመላሽ፣ ታምራት ቶላ እና አባዲ ሐዲስ ሲፎካከሩ፣ በእሑዱ የሴቶች ማራቶን ፍጻሜ ትዕግሥት ቱፋ፣ ማሬ ዲባባና ትርፊ ፀጋዬ ይወዳደራሉ፡፡

የዓርብ ተወዳዳሪ አትሌቶች ነሐሴ 3 ቀን ሪዮ የገቡ ሲሆን፣ የቅዳሜና እሑድ ተፎካካሪዎች ነሐሴ 4 ቀን ወደ ሥፍራው እንደሚያቀኑ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው አስታውቋል፡፡

አነጋጋሪው ዕድሜ

የሪዮ ኦሊምፒክ ከመጀመሩ በፊት ኢትዮጵያን በሚወክሉ አትሌቶች መረጣ ብዙ ማከራከሩ አይዘነጋም፡፡ በተለይ ኢትዮጵያ በረጅሙ ርቀት ካላት ታሪክ ጋር በተያያዘ ትክክለኛውን አትሌት ወደ ሥፍራው ለመላክ ሽኩቻ መፍጠሩ ይታወሳል፡፡

ዛሬ ወደ ሪዮ ከሚጓዙት የአሥር ሺሕ ሜትር ርቀት ተወዳዳሪ አትሌቶች ውስጥ በግንቦት ወር ቻይና ሻንጋይ ላይ በተደረገ የዳይመንድ ሊግ ዓለም አቀፍ ውድድር የተሳተፈው ወጣቱ አባዲ ሐዲስ ተጠቃሽ ነው፡፡ አትሌቱ በዳይመንድ ሊግ ሲሳተፍ በ17 ዓመት ዕድሜ መወዳደሩ ይታወሳል፡፡

ባለፈው ግንቦት በሻንጋይ በተደረገው የ5000 ሜትር ውድድር ላይ 13 ደቂቃ ከ02.49 ሰከንድ በመግባት አራተኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቋል፡፡ በውድድሩ ላይ ያመጣው ሰዓት ከቀድሞ አትሌቶች ቀነኒሳ በቀለና ኢብራሂም ጄላን የተሻለ ስለነበር ለሪዮ መመረጥ ችሏል፡፡

በዕለተ ቅዳሜ ነሐሴ 7 ቀን 2008 ዓ.ም. በሚደረገው የ10,000 ሜትር ፍጻሜ ውድድር ላይ ይግረም ደመላሽ፣ ታምራት ቶላና አባዲ ሐዲስ ቀዳሚ ተሰላፊዎች ተደርገው ተይዘዋል፡፡ በሻንጋይ 5,000 ሜትር ውድድር 17 ዓመት የሚታወቀው አባዲ አሁን የ19 ዓመት ወጣት ተደርጎ ኢትዮጵያን እንደሚወክላት እየተገለጸ ይገኛል፡፡ ግንቦት ወር ላይ በ17 ዓመት የተወዳደረው አባዲ እንዴት አሁን በ19 ዓመት ተደርጎ ተወስዶ ሊወዳደር ይችላል? የሚለው የብዙዎቹ ጥያቄ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ማኅበር አይኤኤኤፍ እንደሚያስቀምጠው፣ የ10,000 ሜትር ደንብ ከሆነ በኦሊምፒክ አንድ አትሌት ከ19 ዓመት በታች ከሆነ ውድድር ላይ መሳተፍ እንደማይችል የተለያዩ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡

ለዚህም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጠባባቂ ባልያዘበት የ10,000 ሜትር ውድድር የዕድሜ ማጣራት ተደርጎ አትሌትውን ከውድድሩ ውጪ ሊሆን ይችላል የሚለው ሐሳብ በብዙዎቹ ዘንድ ሥጋት ፈጥሯል፡፡

ፌዴሬሽኑ በበኩሉ በአትሌቱ ላይ የተነሳው የዕድሜ ችግር ከዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ማኅበር ጋር በመነጋገር ተስተካክሏል ሲል በቅደም የሪዮ ዝግጅት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አብራርቷል፡፡

የብሔራዊ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ስለሺ ብስራት ለሪፖርተር ከሪዮ በማኅበራዊ ድረ ገጽ እንደተናገሩት ከሆነ፣ አባዲ በ19 ዓመት እንደተመዘገበና መቶ በመቶ ውድድር ላይ እንደሚሳተፍ ከስፍራው አረጋግጠዋል፡፡

የረዥም ርቀት አሠልጣኝ ቶሌራ ዲንቃ አትሌቶቹ ለውድድሩ በቂ ዝግጅት እንዳደረጉ ተናግረው ስለ አባዲ የተነገረው የዕድሜ ጉዳይ ፌዴሬሽኑ ከአይኤኤኤፍ ጋር ተነጋግሮ መፍትሔ ላይ እንደደረሰ አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ካላት የረዥም ርቀት ውጤት አንፃር በዚህ ወቅት አንደዚህ ያልተጣሩና መፍትሔ የሚሹ ጉዳዮች በመነሳታቸው ብዙዎችን ቅር አሰኝቷል፡፡ በተለይ በአሥር ሺሕ ሜትር ኢትዮጵያ በእንግሊዛዊው ሞፋራህ የተወሰደባትን ብልጫ ስፖርት ቤተሰቡን እንዲሁም የቀድሞ አትሌቶችን ያስቆጨ ክስተት ነበር፡፡ በእንደዚህ ዓይነት ወቅት ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የሚከተለው መንገድ በተደጋጋሚ ችግር ሲስተዋልበት ይታያል፡፡ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ በቡድን ውስጥ ልምድ ያላቸውን አትሌቶች እንዲሁም ተተኪ አትሌቶችን አጣጥሞ ለውድድር መዘጋጀት ዋነኛ ሥራ እንደሆነ ባለሙያዎች በተለያየ አጋጣሚ ሲናገሩ ይደመጣል፡፡

ኢትዮጵያ በምታደርጋቸው ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድሮች ከዕድሜ ጋር በተያያዘ ከፍተኛ ችግርና መስተጓጎል ሲደርስ ይስተዋላል፡፡ በዚህም መሠረት ዘንድሮ ደቡብ አፍሪካ ደርባን ከተማ ላይ በተደረገው የወጣቶች ሻምፒዮና ላይ ትክክለኛ ዕድሜ ያላቸውን አትሌቶች በቴክኒካል ባለሙያዎች ባለመስተካከሉ 19 አትሌቶች ከኤምባሲ ሳይፈቀድላቸው ቀርቶ አራት አትሌቶች ብቻ ተስተካክሎላቸው ወደ ውድድሩ ማምራታቸው የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡ ቀሪዎቹ 15 ተወዳዳሪዎች ግን በሌሎች ተተክተው ወደ ስፍራው ቢያመሩም፣ ዘጠኙ አትሌቶች ደርባን ላይ ባልተለመደ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ታሪክ በዚያው መቅረታቸው ይታወሳል፡፡ ለዚህም ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በአግባቡ አትሌቶችን ለውድድር ያለመ ቅርብ ችግር እንደሆነ ይነገራል፡፡ በመጨረሻም ምንም እንኳ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የአባዲን ጉዳይ ከዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ማኅበር ጋር ተነጋግሬያለሁ ቢልም ልምድ ያላቸው አትሌቶችን በተጠባባቂነት እንኳን ይዞ ባለመጓዝ ቅሬታ ያስነሳ ጉዳይ ሆኗል፡፡

Standard (Image)

በኢትዮ ትሬያል የተራራ ሩጫ የተሳታፊ ቁጥር ጨምሯል

$
0
0

ለሦስተኛ ጊዜ በአብጃታ ሻላ ሐይቆች ብሔራዊ ፓርክ ነሐሴ 1 ቀን 2008 ዓ.ም. በተካሄደው የኢትዮ ትሬያል የተራራ ሩጫ በርካታ የውጪ አትሌቶችና የአገር ውስጥ ተሳታፊዎች ተገኝተውበታል፡፡

በሦስት ርቀቶች ለማካሄድ ቢታቀድም በዕለቱ የነበረው የአየር ሁኔታ አለመመቻቸት ምክንያት በ21 ኪሎ ሜትርና በ12 ኪሎ ሜትር ውድድሮች ተወስኗል፡፡ የማረሚያ ቤቱ ተወዳዳሪ ኤፋ በልዳ ለሦስተኛ ጊዜ አሸናፊ ሲሆን፣ ታምራት ሽፈራውና ተሾመ ሹሜ ሁለተኛና ሦስተኛ በመሆን አጠናቀዋል፡፡

በሴቶች ልቅና አምባው በአንደኝነት እንዲሁም ፀዳለ ገብረፃድቅና ሐረገወይን አጎናፍር በተከታታይ ደረጃ በመያዝ አሸናፊ ሆነዋል፡፡ ለውድድር አሸናፊዎቹ የ20,000፣ 12,000 እና የ8,000 ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡

በውድድሩ የስፔን፣ የጀርመንና የደቡብ አፍሪካ እንዲሁም የሩሲያ ሯጮች ተሳታፊ ነበሩ፡፡ ሩጫው አብጃታ ሻላ ሐይቆችና ብሔራዊ ፓርክ ከተደቀነበት የመድረቅና የመጥፋት አደጋ መከላከል ከሚለው ጎን ለጎን፣ የስፖርት ቱሪዝምን በአገሪቱ ለማስፋፋት ያለመ መሆኑ የሪያ ኢትዮጵያ ስፓርትስ ቦርድ ሰብሳቢ ገብረእግዚአብሔር ገብረማርያም ተናግሯል፡፡

እንደ ገብረእግዚአብሔር ገለጻ ከሆነ፣ እንደዚህ ዓይነት ውድድሮችን ማካሄድ ኢትዮጵያ በአገር አቋራጭ ያላትን ተሳትፎ ከፍ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል፡፡ ከውድድሩ በኋላ በተደረገው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ‹‹በዚህ ተፈጥሮአዊ ቦታ ላይ እንደዚህ ዓይነት ውድድሮች ማድረግ በኢትዮጵያ ያለው ተፈጥሯዊ መስህብ የቱሪዝም ዕድገት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ትልቅ ነው፤›› ያሉት የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሰለሞን ታደሰ ናቸው፡፡

886 ስኩዌር ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የአብጃታ ሻላ ሐይቆችና ብሔራዊ ፓርክ አደጋ ላይ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ በየዓመቱ በሚደረገው ዓመታዊ ውድድር የአካባቢው ነዋሪ አስፈላጊውን እንክብካቤ እንዲያደርግ መነቃቃት እንደሚፈጥር የኢትዮ ትሪስ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ቃለአብ ጌታነህ አብራርተዋል፡፡

በየዓመቱ የሚደረገው የተራራ ላይ ሩጫ ኬንያና ደቡብ አፍሪካ ላይ ከሚደረገው ውድድር በኢትዮጵያም እየተለመደ መምጣት እንዳለበት ገብረእግዚአብሔር አክሏል፡፡

 

Standard (Image)

የፋጡማ ሮባና የቲኪ ገላና ድልን የሚሠልሰው ማን ነው?

$
0
0

ኢትዮጵያውያት የሚጠበቁት የሴቶች ማራቶን ውድድር ነሐሴ 8 ቀን 2008 ዓ.ም. ከቀኑ 9፡30 ይደረጋል፡፡ በውድድሩም ትዕግሥት ቱፋ፣ ማሬ ዲባባና ትርፊ ፀጋዬ ይሳተፋሉ፡፡

ለመጀመርያ ጊዜ በኦሊምፒክ የሚሳተፉት አትሌቶች ከፍተኛ ፉክክር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡ ከፍተኛ ልምድ ያላት ማሬ ዲባባና የቅርቦቹ አትሌቶች የሚያደርጉት ውድድር በብዙዎች ዘንድ ተጠባቂ ያደርጋቸዋል፡፡ በተለይ ማሬ እ.ኤ.አ. በ2015 በቻይናዋ ቤጂንግ በተካሄደው የዓለም ሻምፒዮና በማራቶን የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘችው ርቀቱን 2 ሰዓት 27 ደቂቃ ከ39 በመግባት ነበር፡፡

 ሌላዋ ተፎካካሪ ትዕግሥት ቱፋ በ2014 ሻንጋይ ማራቶን የራስዋን ሪከርድ ያሰፈረች ሲሆን፣ ውድድሩን 2 ሰዓት ከ21 ደቂቃ ከ52 በመጨረስ ልምድም ያገኘችበት ውድድር ነው፡፡ ለሪዮ ኦሊምፒክ እንድትመረጥ ያስቻላትን ውጤት ያገኘችው በ2015  ለንደን ማራቶን 2 ሰዓት ከ23 ደቂቃ ከ22 በመግባት ማሸነፏ ነው፡፡ አትሌቷ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ሴት የረዥም ርቀት አትሌቶች ተስፋ ተጥሎባታል፡፡

ሌላኛዋ አትሌት ትርፊ ፀጋዬ ምርጥ ጊዜዋ ትርፊ 2 ሰዓት ከ20 ደቂቃ ከ18 ሰከንድ በ2014 የበርሊን ማራቶን ላይ ያጠናቀቀችበት ሲሆን፣ የፓሪስና የቶኪዮ የማራቶን አሸናፊ ነበረች፡፡ በዘንድሮ የሪዮ ኦሊምፒክ ላይ የተቻላትን ጥረት አድርጋ ስሟን በኦሊምፒክ ማስፈር እንደምትፈልግ ተናግራለች፡፡

ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ ተሳትፎዋ እ.ኤ.አ. በ1996 በአትላንታ ሴቶች ማራቶን ፋጡማ ሮባ 2 ሰዓት ከ26 ደቂቃ ከ05 በመግባት የመጀመርያውን ወርቅ አምጥታለች፡፡ ከዚያ በኋላ በሴቶች ማራቶን በኦሊምፒክ ወርቅ ለማምጣት አራት ኦሊምፒያድ ወስዷል፡፡ በቲኪ ገላና አማካይነት በ2012ቱ የለንደን ኦሊምፒክ ወርቅ ተመዝግቧል፡፡ ከአራት ዓመት በፊት በለንደን ጎዳና ላይ በተደረገው ውድድር ቲኪ ርቀቱን 2 ሰዓት ከ23 ደቂቃ ከ07 በመፈጸም የኦሊምፒክ ሪከርድ መስበሯ ይታወሳል፡፡

በዘንድሮም የሪዮ ኦሊምፒክ ከፋጡማና ቲኪ ቀጥሎ ሦስተኛዋ ኢትዮጵያዊት ባለድል ማን ትሆን?

 

 

 

Standard (Image)

አዲሷ ክስተት አልማዝ አያና

$
0
0

- የ10,000 ሜትር የ23 ዓመት የዓለም ክብረወሰን የሰበረችበት ሪዮ ኦሊምፒክ

ኢትዮጵያዊቷ አልማዝ አያና የዓለምን ክብረ ወሰን በመስበር የሪዮ ኦሊምፒክን 10,000 ሜትር ውድድር አሸነፈች፡፡ በዓለም ከታዩት እጅግ አስደናቂ የረዥም ርቀት ውድድሮች አንዱ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

ነሐሴ 6 ቀን 2008 ዓ.ም. በተካሄደው የሪዮ ኦሊምፒክ የሴቶች 10,000 ሜትር ፍጻሜ አልማዝ አያና 29 ደቂቃ 17.45 ሰከንድ በመሮጥ ነው ከዓለም ክብረ ወሰን ጋር ያሸነፈችው፡፡

ከመነሻው ጀምሮ በጥንቃቄና በራስ መተማመን መንፈስ በሁለተኛነት ትከተል የነበረችው አልማዝ፣ ከ12 ዙር በኋላ መሪነቱን በመጨበጥና ተከታዮቿን በርቀት በማለፍ በአስደናቂ አሯሯጥ ምልዐተ ኃይሏን በመጠቀም በ300 ሜትር ልዩነት ለማሸነፍ ችላለች፡፡

አልማዝ ከ23 ዓመት በፊት በ1985 ዓ.ም. በቻይናዊቷ ዋንግ ዡንዣ እስከ አሁን ተይዞ የነበረውን 29፡31.78 በ14 ሰከንድ ሰብራዋለች፡፡ በውድድሩ ሌላዋ ኢትዮጵያዊት የሁለት ኦሊምፒክ ባለወርቋና ባለአንድ ነሐሷ ጥሩነሽ ዲባባ በ29፡42.56 ደቂቃ ሦስተኛ ሆና ነሐስ ስትሸለም፣ የአምናው የዓለም ሻምፒዮናዋ ኬንያዊቷ ቪቪያን ቼሩየት በ29፡31.78 በሁለተኛነት ብሩን አግኝታለች፡፡

ጥሩነሽ የመጀመርያዎቹን ዙሮች ትመራ የነበረውን ኬንያዊት አሊስ አፕሮትን አስከትላ በሦስተኛነት የገባችበት ጊዜ፣ ከስምንት ዓመት በፊት በቤጂንግ ኦሊምፒክ ነባሩን የኦሊምፒክ ሪከርድ ስትሰብር ካስመዘገበችው በ12 ሰከንድ የፈጠነ ነው፡፡

አልማዝ ያሁኑ የሪዮው አዲሱ የኦሊምፒክ የ10,000 ሜትር ድሏ ከዓለም ክብረ ወሰን ጋር የተገናኘው ለሁለተኛ ጊዜ ባደረገችው ሩጫዋ ነው፡፡

ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ ታሪክ በሴቶች በ10,000 ሜትር ያገኘችውን ወርቅ በአልማዝ አማካይነት አምስት ላይ ደርሷል፡፡ የመጀመርያዋ አሸናፊ ደራርቱ ቱሉ በባርሴሎና እና በሲድኒ፣ እንዲሁም ጥሩነሽ ዲባባ በቤጂንግና በለንደን ሁለት ሁለት ወርቅ ማግኘታቸው ይታወሳል፡፡

ባለፉት 50 ዓመታት በ10,000 ሜትር ሴቶች የዓለም ክብረ ወሰንን ያስመዘገቡት አውሮፓውያንና አሜሪካውያን እንዲሁም አንዲት ቻይናዊት ሲሆኑ፣ ዘንድሮ ለመጀመርያ ጊዜ የ24 ዓመቷ ኢትዮጵያዊት አልማዝ አያና አፍሪካን የክብሩ ተቋዳሽ አድርጋለች፡፡ አልማዝ በቀደምት የውድድር ተሳትፎዋ የ3,000 ሜትር መሠናክል፣ 3,000 ሜትርና 10 ኪሎ ሜትር ሯጭ ነበረች፡፡

‹‹የዓለማችን ክስተት››

አልማዝ እ.ኤ.አ. በ2013 በሞስኮ በተካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ5,000 ሜትር በሦስተኛነት የነሐስ ሜዳሊያ በመሸለም የስኬት ጉዞዋን ጀምራለች፡፡ አምና በቤጂንግ በተካሄደው የዓለም ሻምፒዮና ገንዘቤ ዲባባን በማሸነፍ ወርቅ ማጥለቋ ይታወሳል፡፡ በአህጉራዊ ውድድር የመጀመርያውን ድሏን ያጣጣመችው በ2014 በማራካሽ (ሞሮኮ) በተከናወነው የ5,000 ሜትር ውድድር ታዋቂዋን ገንዘቤ ዲባባ በመርታት ነበር፡፡ ከአንድ ወር በኋላ በማራካሽ ስታዲየም በተደረገው በአህጉሮች መካከል በሚደረገው የዓለም አትሌቲክስ ዋንጫ በ5,000 ሜትር ለአፍሪካ የወርቅ ሜዳሊያ አስገኝታለች፡፡

በ5,000 ሜትርም የምትሮጠው አልማዝ በዳይመንድ ሊግ አምና በሻንጋይ ሲካሄድ ያስመዘገበችው 14፡14.32 የዓለም ሦስተኛው ፈጣን ሯጭ አሰኝቷታል፡፡ ሁለቱ ቀዳሚዎች በ14፡11.5 የዓለም ክብረወሰን ባለቤቷ ጥሩነሽ ዲባባና መሠረት ደፋር ናቸው፡፡ ባለፈው ግንቦት በሮም በተካሄደው ዓለም አቀፍ ውድድርም 14፡12.59 በሆነው ጊዜ በማሸነፍ ከጥሩነሽ ቀጥላ ሁለተኛዋ ፈጣን አትሌት ለመሆን በቅታለች፡፡

የኢትዮጵያን የኦሊምፒክ ተወዳዳሪዎች ለመለየት ከአንድ ወር ተኩል በፊት በሔንግሎ በተካሄው የ10,000 ሜትር ውድድር ጥሩነሽ ዲባባን ያሸነፈችው አልማዝ በዘንድሮው ኦሊምፒክ ያስመዘገበችው በዓለም ክብረወሰን የታጀበው ድሏ ከፍተኛ አድናቆት አትርፎላታል፡፡ የቀድሞው የኦሊምፒክ ሜዳሊያ ተሸላሚ ብሬንዳን ፎስተር በቢቢሲ የኦሊምፒክ ዘገባ ላይ ሲተነትን አልማዝን ‹‹የዓለማችን ክስተት›› ብሏታል፡፡

አስደናቂውን የ10,000 ሜትር ሩጫ ሲተነትን የነበረው ሌላው ተነታኝ ‹‹በዚህኛው ውድድር እንዲህ ያሳየችን በቀጣዩ የ5,000 ሜትር ሩጫዋ ምን ታሳየን ይሆን?›› ብሏል፡፡ አልማዝ የ5,000 ሜትር ማጣሪያ ውድድርን ማክሰኞ ነሐሴ 10 ቀን ካደረገች በኋላ ፍጻሜው ዓርብ ነሐሴ 13 ቀን ይሆናል፡፡

በኦሊምፒክ ደረጃ ሠንጠረዥ ኢትዮጵያ እስከ ዓርብ ምሽት ድረስ አልማዝ አያናና ጥሩነሽ ዲባባ ባስገኙት 1 ወርቅና 1 ነሐስ ሜዳሊያዎች  በ29ኛ ደረጃ ላይ ስትገኝ፣ አሜሪካ በ16 ወርቅ፣12 ብርና 10 ነሐስ ቀዳሚውን ሥፍራ ተቆናጣለች፡፡

Standard (Image)

የቀድሞው የፊፋ ፕሬዚዳንት ጆአዎ ሃቨላንጅ በ100 ዓመታቸው አረፉ

$
0
0

የቀድሞው የፊፋ ፕሬዚዳንት ጆአዎ ሃቨላንጅ በ100 ዓመት ዕድሜያቸው ነሐሴ 10 ቀን 2008 ዓ.ም. በሪዮ ዲጄኔሮ ሳማሪታኖ ሆስፒታል አረፉ፡፡

ብራዚላዊው ሃቨላንጅ የዓለምን እግር ኳስ የሚመራው አካል ፊፋን እ.ኤ.አ. 1974 እስከ 1998 ድረስ አገልግለውታል፡፡ እንደ ቢቢሲ ዘገባ በአመራር ላይ በነበሩበት ጊዜ በፊፋ ውስጥ በነበረ የአሠራር ክፍተትና ብልሽት ዙሪያ በሚያዝያ 2005 ዓ.ም. የተደረገው ምርመራ ይፋ መሆኑን ተከትሎ ከፊፋ የክብር ፕሬዚዳንትነት ራሳቸውን ማግለላቸው በዓመቱም በሳምባ ምች ታመው ሆስፒታል መግባታቸው ይታወቃል፡፡

ሃቨላንጅ በኢንተርናሽናል ኦሊምፒክ ኮሚቴ አባልነት እ.ኤ.አ. 1963 በጤና እክል ሳቢያ ራሳቸውን እስካገለሉበት 2011 ድረስ አባል ነበሩ፡፡ ሚያዝያ 30 ቀን 1908 ዓ.ም. የተወለዱትና ድንቅ ዋናተኛ የነበሩት ሃቨላንጅ፣ ከ80 ዓመት በፊት በ1936 በተደረገው የበርሊን ኦሊምፒክ በ400 ሜትርና በ1,500 ሜትር ነፃ ዋና ተወዳድረው ነበር፡፡ ከ64 ዓመት በፊት በ1952 በተደረገው የሔልሲንኪ ኦሊምፒክ የውኃ ላይ ኳስ ጨዋታ (ወተር ፖሎ) ቡድን ውስጥም ነበሩበት፡፡

አውሮፓውያን በፊፋ ውስጥ የነበራቸው ገደብ የሌለው የበላይነት ያልተደሰቱት አፍሪካና እስያ በኢትዮጵያ አስተባባሪነት እንግሊዛዊውን የፊፋ ፕሬዚዳንት ሰር ስታንለይ ሮውስን በድምፅ ቀጥተው ሃቨላንጅ መንበሩን እንዲቆናጠጡ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡

ለ24 ዓመታት ፊፋን ሲመሩ መሠረታዊ ለውጥ እንዳደረጉ የሚነገርላቸው ሃቨላንጅ አንዱ ተግባራቸው የዓለም ዋንጫ ተካፋይ አገሮች ቁጥር ወደ 32 ማድረሳቸውና የአፍሪካ፣ የእስያና ኦሺያና ኮታ ከፍ ማድረጋቸው ነው፡፡ ካሜሩን በ1982 ዓ.ም. በዓለም ዋንጫ ለሩብ ፍጻሜ በመግባት የመጀመሪያዋ አፍሪካዊት መሆን የቻለችበትም ጊዜ ነበር፡፡

ፊፋ በድረ ገጹ እንዳወሳው፣ ሃቨላንጅ ሰኔ 4 ቀን 1966 ዓ.ም. የፊፋን ፕሬዚዳንትነት ከተቆናጠጡ በኋላ በስድስት ዙር የአመራርነት ጉዟቸው 50 አዲስ ፌዴሬሽኖች (ማኅበሮች) የዓለምን እግር ኳስ በሚመራው አካል ውስጥ አባል ሆነዋል፡፡ ፊፋ የዓለም ሴቶች እግር ኳስ ዋንጫን ማዘጋጀት የጀመረበት 1983 ዓ.ም. በርሳቸው ፕሬዚዳንትነት ዘመን ነበር፡፡ እንዲሁም የዓለም ወጣቶች ዋንጫ (ከ20 ዓመት በታች)፣ የዓለም ታዳጊዎች ዋንጫ (ከ17 ዓመት በታች)፣ እንዲሁም የመጀመሪያው የፉትሳል ውድድር እንደቅደም ተከተላቸው በ1969 ዓ.ም.፣ በ1977 ዓ.ም. እና በ1981 ዓ.ም. አስጀምረዋል፡፡  

ጆአዎ ሃቨላንጅ ከኢትዮጵያ ጋር በተለይ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ፕሬዚዳንት ከነበሩት ኢትዮጵያዊው ይድነቃቸው ተሰማ ጋር ቁርኝት ነበራቸው፡፡ ከ44 ዓመት በፊት ለፊፋ ፕሬዚዳንትነት ሲወዳደሩ የአፍሪካውያንን ድምፅ ለማግኘት የሚያስችላቸው ድምፅ የሚያገኙት በይድነቃቸው ተሰማ ፊታውራሪነት መሆኑን በመተማመን ከቅስቀሳ ቡድናቸው ጋር በመጀመሪያ ጎራ ያሉት አዲስ አበባ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ፉትቦል ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት በመገኘት መወያየታቸው ይታወሳል፡፡

ብራዚል ከሁለት ዓመት በፊት ያስተናገደችውን የዓለም ዋንጫ በ98 ዓመታቸው ከቤታቸው ሆነው የተከታተሉት ሃቨላንጅ እየተካሄደ ያለውን የሪዮ ኦሊምፒክ በሕይወት እያሉ አይተውታል፡፡ አልማዝ አያና አስደናቂውን የ10,000 ሜትር ድሏን ያጣጣመችበት የኦሊምፒክ ስታዲየም በሃቨላንጅ ስም የሚጠራ ነው፡፡

ከሦስት አሠርታት በፊት ጋዜጠኞች ‹‹ከርስዎ በኋላ የፊፋ ፕሬዚዳንት ማን ይሆናል?›› ብለው ለጠየቋቸው የሰጡት ምላሽ ባጭር ቋንቋ ‹‹ሚስተር ተሰማ ነዋ!›› ብለው በወቅቱ የካፍ ፕሬዚዳንት የነበሩት ይድነቃቸው ተሰማ (1914 - 1979) ለቦታው እንደሚመጥኑ ተናግረው ነበር፡፡ ይኽንኑ ተከትሎ በወቅቱ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ጥያቄ ያቀረበላቸው አቶ ይድነቃቸው፣ ለሃቨላንጅ ጥቆማ አክብሮታቸውን ገልጸው፣ በጤና ምክንያት እንደማያስቡት መናገራቸው ይታወሳል፡፡ ዓመት ሳይቆዩ አቶ ይድነቃቸው ነሐሴ 13 ቀን 1979 ዓ.ም. ማረፋቸው አይረሳም፡፡ የታሪክ ግጥምጥሞሽ ሆነና ሁለቱም ያረፉት በተመሳሳይ ወር ሆነ፡፡ ሃቨላንጅ ያረፉት ነሐሴ 10 ቀን (ኦገስት 16) ሲሆን፣ ይድነቃቸው ያረፉት ነሐሴ 13 ቀን (ኦገስት 19) ነበር፡፡    

Standard (Image)

አልማዝ በአምስት ሺሕ ሜትር ፍጻሜ ትጠበቃለች

$
0
0

አሥራ አንደኛ ቀኑን በያዘው የሪዮ ኦሊምፒክ የኢትዮጵያ በሴቶች ውጤታማ ጉዞን እያሳየች ትገኛለች፡፡ በተለይ ሴቶቹ ከወንዶቹ የተሻለ ውጤትን በረዥም ርቀቱም ሆነ በአጭር ርቀቱ ኃላፊነታቸው ሲወጡ ተስተውሏል፡፡

ከነሐሴ 6 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ውድድር ማድረግ የጀመረችው ኢትዮጵያ በ10ሺሕ ሜትር የዓለምን ክብረ ወሰን መስበር ከቻለችው አልማዝ አያና ጀምሮ በሴቶች 1,500 ገንዘቤ ዲባባ፣ በማራቶን ማሬ ዲባባና ትርፊ ፀጋዬ እንዲሁም በ5,000 ሜትር ግማሽ ፍጻሜ አልማዝና ሰንበሬ ተፈሪ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ተወጥተዋል፡፡ ባለፈው እሑድ በተደረገው የማራቶን ውድድር ማሬ ዲባባ በሦስተኝነት የነሐስ ሜዳሊያ ስትሸለም ትርፊ 4ኛ ሆናለች፡፡ ድሉን ኬንያዊቷ ጂሚማ ሳምጎንግ አጣጥማዋለች፡፡

በወንዶቹ አሥር ሺሕ ሜትር ከዓለም ክብረ ወሰን ባለቤቱ ሞ ፋራ ጋር በመተናነቅ 27 ደቂቃ ከ06 ሰከንድ ከ26 በመጨረሻ የነሐስ ተሸላሚ ከሆነው ታምራት ቶላ በስተቀር እምብዛም በወንዶቹ አመርቂ ውጤት አልታየም፡፡ በወንዶች 800 ሜትር መሐመድ አማን የመጀመሪያውን ማጣሪያ ቢያልፍም የመጨረሻውን ምድብ መድረስ አልቻለም፡፡ በ1500 ሜትር እንኳ በሴቶች ገንዘቤ ዲባባ፣ በሶ ሳዶ እንዲሁም ዳዊት ስዩም ከየምድባቸው በቀጥታ ማለፍ ችለዋል፡፡ በወንዶች አማን ወጤ፣ መኮንን ገብረመድህንና ዳዊት ወልዴ አማን ባጋጠመው ጉዳት ከውድድሩ ሲወጣ፣ ዳዊት ወልዴ 3 ደቂቃ ከ33.29 በማጠናቀቅ እንዲሁም መኮንን ገብረመድህን 3 ደቂቃ 47 ሰከንድ ከ33 በሆነ ውጤት ከምድቡ የተሻለ ሰዓት ስለነበረው ለግማሽ ፍጻሜ የደረሱ አትሌቶች ሆነዋል፡፡

በዚህም መሠረት ዳዊትና መኮንን ሐሙስ ነሐሴ 12 ቀን 2008 ዓ.ም. ኢትዮጵያን በመካከለኛው ርቀት የሚወክሏት ይሆናል፡፡ ዓርብ ነሐሴ 13 ቀን የሚደረገው የ5000 ሺሕ ሜትር ፍጻሜ ውድድር ኢትዮጵያውያቱ ከወዲሁ ትልቅ ግምት አግኝተዋል፡፡

ሐምሌ 10 ቀን በተደረገው የሴቶች 5000 ሜትር ማጣሪያ ውድድር የ10ሺሕ ሜትር ባለሪከርድ አልማዝ አያናና ሰንበሬ ተፈሪ እንዲሁም አባብል የሻህ የተወዳደሩ ሲሆን፣ አልማዝ በተለምዶ ብቃቷ 15 ደቂቃ ከ04 ሰከንድ 35 አንደኛ በመሆን በሰፊ ርቀት አጠናቃለች፡፡ ሌላዋ ኢትዮጵያዊት ሰንበሬ ተፈሪ ደግሞ 15 ደቂቃ ከ17 ሰከንድ ከ43 ሁለተኛ ስትሆን፣ ኬንያዊዋ ቪቪያን ቼሮየት 15 ደቂቃ ከ17 ሰከንድ ከ74 በመጨረስ ሦስተኛ ደረጃ በመያዝ ማጠናቀቅ ችላለች፡፡

አልማዝ ከወዲሁ በ5000 ሺሕ ሜትርም ለአገሯ ወርቅ እንደምታመጣ እየተነገረ ይገኛል፡፡ በተለይ አትሌቷ ከ3000 ሜትር መሠናክል  ወደ ቀጥታ ሩጫ ውድድር ከመጣች በኋላ በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤታማ እየሆነች መጥታለች፡፡ ለዚህም ደግሞ በ10 ሺሕ ሜትር ለመጀመሪያ ጊዜ በሪዮ ላይ ተገኝታ የዓለም ሪከርድ መስበር መቻሏ ትልቅ ግምት እንዲሰጣት አስችሏል፡፡

የ24 ዓመቷ አልማዝ ወደ ረዥም ርቀቱ ከመግባቷ በፊት በ3000 ሜትር 8 ደቂቃ ከ22 ሰከንድ ከ22 በመግባት የራሷን ጥሩ ሰዓት ያስመዘገበች ሲሆን፣ በ500 ሜትር ደግሞ እ.ኤ.አ. 2015 ቤጂንግ ላይ በተደረገው አይኤኤፍ ዓለም ሻምፒዮና የ1500  የሪከርድ ባለቤት ገንዘቤ ዲባባን በመርታት 14 ደቂቃ ከ26 ሰከንድ ከ83 ያጠናቀቀችበት የቅርብ ትውስታ ነው፡፡

ሌላዋ ኢትዮጵያን በመወከል ከአልማዝ ጎን የምትሰለፈው ሰንበሬ ተፈሪ ነች፡፡ አትሌቷ 1500 ሜትርና በአገር አቋራጭ ውድድር ላይ በመሳተፍ ትታወቃለች፡፡ በተለይ ስንበሬ ጉያንግ ቻይና ላይ ባደረገችው ዓለም አቀፍ አገር አቋራጭ ውድድር ላይ 26 ደቂቃ ከ26 ሰከንድ በመግባት የብር ሜዳሊያና በተመሳሳይ ሁኔታ በ5000 ሜትር ቤጂንግ በተደረገው ውድድር አልማዝን በመከተል ርቀቱን 14 ደቂቃ ከ44 ሰከንድ ከ07 በመጣበት የብር ሜዳሊያ ተሸላሚ መሆንዋ ይታወሳል፡፡ ሦስተኛዋ ተዳዳሪ አባብል የሻነህ፣ በማጣሪያው 15 ደቂቃ ከ24 ሰከንድ ከ38 በመግባት ወደ ፍጻሜው ማለፍ ችላለች፡፡ ኬንያዊቷ ቪቪያን ቼሮየት ማጣሪያውን ያለፈች ስትሆን፣ ባለፈው ዓርብ በተደረገው የ10 ሺሕ ሜትር ፍጻሜ ከወሊድ መልስ ርቀቱን 29 ደቂቃ ከ32፡53   ሰከንድ በመጨረስ ሁለተኛ ሆና መጨረሷ ይታወሳል፡፡ ዓርብ ከቀኑ 9 ሰዓት ከ40 ደቂቃ በሚደረገው 5000 ሜትር ፍጻሜም ላይ ሦስቱ የሚያደርጉት ፉክክር ይጠበቃል፡፡

 

Standard (Image)

የወንዶች ማራቶን - የሪዮ ኦሊምፒክ ማጠቃለያ

$
0
0

-  የኢትዮጵያ አራተኛው ባለድል ይመጣ ይሆን?

ከሁለት ሳምንታት በላይ ያስቆጠረው 31ኛው ኦሊምፒያድ ፍፃሜው ላይ ደርሷል፡፡ በመዝጊያው ነሐሴ 15 ቀን 2008 ዓ.ም. ከሚካሄዱት ውድድሮች ዋነኛው የወንዶች ማራቶን ይጠቀሳል፡፡ ማራቶን ከጥንት እስከዛሬ የብዙዎችን ቀልብ እንደገዛ ነው፡፡ በየኦሊምፒኩ የሚጠበቁ ሯጮች እንደሚያሸንፉ ሁሉ ያልተጠበቁ፣ ያልታሰቡ ክብሩን ሲቀዳጁ ይታያል፡፡ ከእነዚህ አንዱ ባለፈው የለንደን ኦሊምፒክ አሸናፊው ዑጋንዳዊ ስቴፈን ኪፕሮች ተጠቃሽ ነው፡፡

በዛሬው የሪዮ ኦሊምፒክ ማራቶን በተለይ ምሥራቅ አፍሪካውያኑ ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ኬንያና ዑጋንዳ የሚያደርጉት ፉክክር ይጠበቃል፡፡ የኢትዮጵያ ተሰላፊ ሠለስቱ ሯጮች ተስፋዬ አበራ፣ ለሚ ብርሃኑና ፈይሳ ሌሊሳ ናቸው፡፡ ከኢትዮጵያ ሯጮች ፈጣን ሰዓት ያለው ባለፈው ጥር በዱባይ ማራቶን 2፡04፡24  በመፈጸም ያሸነፈው ተስፋዬ አበራ ነው፡፡ ከኬንያውያኑ ኢሉድ ኪፕችግ (2፡03፡05) እና ስታንሌይ ቢዎት (2፡03፡51) ቀጥሎ ዘንድሮ ፈጣን ሰዓት ያስመዘገበው ተስፋዬ፣ ባለፈው ሚያዝያ ባሸነፈው ሀምቡርግ ማራቶን በ2፡06፡58 መፈጸሙ በጥሩ አቋም ላይ እንደሚገኝ የአይኤኤፍ ዘገባ ያመለክታል፡፡ በሌሎች ታላላቅ ውድድሮች ባይወዳደርም በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ሮጧል፡፡

ለሚ ብርሃኑ ከተስፋዬ ቀጥሎ ጥሩ ሰዓት 2፡04፡33 ያስመዘገበ ሲሆን፣ ባለፈው ሚያዝያ የቦስተን ማራቶንን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ማሸነፉ ይነገርለታል፡፡ አምና በቤጂንግ በተካሄደው የዓለም ሻምፒዮና በ15ኛነት ካጠናቀቀበት ውድድር ሌላ በታላላቅ ውድድሮች አልተካፈለም፡፡ ሦስተኛው ተወዳዳሪ ፈይሳ ሌሊሳ ዘንድሮ ምርጥ ሰዓት ካላቸው ሁለት ኬንያውያንና ሁለት ኢትዮጵያውያን ተርታ ውስጥ ባይገባም ወቅታዊ ሰዓቱ 2፡06፡56 ነው፡፡

በዓምናው የዓለም ሻምፒዮና በቤጂንግ ሳይጠበቅ ኢትዮጵያዊውን የማነ ፀጋይን አስከትሎ ያሸነፈው ኤርትራዊው ግርማይ ገብረሥላሴ ዘንድሮም ውጤታማ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል፡፡ በማራቶን የዓለም ሻምፒዮን ሆኖ የኦሊምፒክ ባለድል እስኮሁን አልተመዘገበም፡፡ ቀደም ባሉት ኦሊምፒኮች የሲዲኒው አሸናፊ ገዛኸኝ አበራና የለንደኑ ስቴፈን ኪፕሮች የዓለም ሻምፒዮን የሆኑት ከኦሊምፒክ ድሎቻቸው በኋላ ነበር፡፡ ዘንድሮ ይህን ታሪክ የሚለውጥ ይኖር ይሆን?

ኢትዮጵያና ማራቶን

ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በኦሊምፒክ መድረክ ከ60 ዓመታት በፊት ስትገኝ፣ ከተወዳደረችባቸው ስፖርቶች አንዱ የአትሌቲክሱ ማራቶን ነበር፡፡ በኅዳር 1949 ዓ.ም. በተካሄደው ውድድር የሮጡት ባሻዬ ፈለቀና ገብሬ ብርቄ ነበሩ፡፡ ባሻዬ 29ኛ፣ ገብሬ 32ኛ ሆነው ማጠናቀቃቸው እ.ኤ.አ. የ1956 ሜልቦርን ኦሊምፒክ ሰነድ ያወሳል፡፡

ኢትዮጵያ ወርቃዊ ድል ማጣጣም የጀመረችው እ.ኤ.አ. በ1960 በሮም ኦሊምፒክ በማራቶን ነበር፡፡ በደማቅዋ የአውሮፓ በጋ ምሽት፣ ጳጉሜን 5 ቀን 1952 ዓ.ም. ጀንበርዋ በሮም ኦሊምፒክ ስታዲየም ጀርባ ባዘቀዘቀችበት አጋጣሚ አንድ ያልታወቀ ጥቁር ገጽታ ያለው አትሌት፣ የማራቶኑን ሩጫ በውራ ጎዳናው በቀዳሚነት ፈፀመ፡፡ በባዶ እግሩ የሮጠው  አበበ ቢቂላ በ2 ሰዓት 16 ደቂቃ 15 ሰከንድ የመጨረሻውን መስመር በጥሶ በማለፍ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ከሁሉም በላይ እንድትውለበለብ አደረጋት፡፡ ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አበበ ዋቅጅራም እንደ አበበ ቢቂላ ሁሉ በባዶ እግሩ ሮጦ በሰባተኛነት አጠናቅቋል፡፡ አበበ ቢቂላ በሮም በሽልማት ሰገነቱ ላይ እንደወጣ የመጀመሪያው «ጥቁር አፍሪካዊ» የኦሊምፒክ ወርቅ ሜዳሊያ አጥላቂ ሆነ፡፡

ከአራት ዓመት በኋላ ለኢትዮጵያ ሦስተኛዋ በሆነው የቶኪዮው የኦሊምፒክ ተሳትፎ፣ አበበ ቢቂላ ጥቅምት 11 ቀን 1957 ዓ.ም. ተጫምቶ በመሮጥ ለሁለተኛ ጊዜ የማራቶን ድሉን አዲስ የዓለምና የኦሊምፒክ ክብረ ሰዓትን በ2 ሰዓት 12 ደቂቃ 11.2 ሰከንድ በመፈጸም መስበሩ ብቻ ሳይሆን፣ የትርፍ አንጀት ቀዶ ሕክምና ባደረገ ስድስት ሳምንት ውስጥ ማሸነፉ ገድሉን ልዩ ያደርገዋል፡፡

ከእርሱ በፊት ማንም ያልፈጸመውን፣ ከእርሱም በኋላ ለ16 ዓመታት ማንም ያላደረገውን የኦሊምፒክ ማራቶን ሁለት ጊዜ አከታትሎ የመውሰድ ገድል ፈጸመ፡፡ ይኸም ብቻ አይደለም ባሻናፊነት የገባበት ሰዓትም እጅግ በጣም ፈጣንና በእንግሊዛዊው ባሲል ሔትሌይ በ2 ሰዓት 13 ደቂቃ 55 ሰከንድ ተይዞ የነበረውን የዓለም ክብረወሰን በ1 ደቂቃ 43፡8 ሰከንድ የሰበረበት ነው፡፡

‹‹እንደበረዶ ነጫጭ ጥርስ አብቅሎ፣ ይቆረጣጥማል ሰዓት እንደቆሎ›› ብለው በወቅቱ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ዋና ጸሐፊ የነበሩት አቶ ይድነቃቸው ተሰማ (1914-1979) እንዲቀኙለት አድርጓቸዋል፡፡

ከ52 ዓመታት በፊት አበበ ቢቂላ ለሁለተኛ ጊዜ ታላቁን ሩጫ ማራቶንን አሸንፎ ወርቅ ሲያጠልቅ ‹‹የበርሊን ማራቶን መጽሔት›› ዘጋቢ እንዲህ ነበር የጻፈው፡፡

‹‹አበበ ቢቂላ በ1952 ዓ.ም. የሮም ኦሊምፒክ ማራቶን በባዶ እግሩ ሮጦ ተአምራዊ አሸናፊ ከሆነ ወዲህ የማራቶንን ሩጫ በ2 ሰዓት ከ14 ደቂቃ የሚጨርስ ቢኖር ሻምፒዮን ይባላል፤ በ2 ሰዓት ከ13 ደቂቃ የሚፈጽም ከተገኘ ደግሞ ድንቅ ሻምፒዮን ይባላል፡፡ አበበ ቢቂላ ግን በቶኪዮ ኦሊምፒክ 2 ሰዓት ከ12 ደቂቃ ከ11፡2 ሰከንድ በማምጣቱ ምን ብዬ እንደምለው ቃላት አጥቼለታለሁ፡፡››

በቀጣዩ አራት ዓመት አበበ ቢቂላ ለሦስተኛው ድል ቢሮጥም፣ 17ኛው ኪሎ ሜትር ላይ ባጋጠመው የጡንቻ መሸማቀቅ አቋርጦ ወጥቷል፡፡ ቢሆንም ድሉ ከኢትዮጵያ አላፈተለከም፡፡ በመስከረም 1961 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ. 1968) የሜክሲኮ ኦሊምፒክ ማሞ ወልዴ አገሩን ለሦስተኛ ጊዜ አሸናፊ ያደረጋትን ድል አስመዘገበ፡፡ መርዓዊ ገብሩም ስድስተኛ ሆነ፡፡ ማሞ በ10,000 ሜትር ሩጫም ከኬንያዊው ናፍታሊ ቲሙ ጋር እልህ አስጨራሽ ፉክክር አድርጎ የብር ሜዳሊያ ለማጥለቅ ችሏል፡፡ የማሞ የማራቶን ድልም ‹‹ማራቶን ማራቶን ማራቶን ልዕልቷ

 አበበና ማሞ ሆኑ ባለቤቷ›› ተብሎ እንዲዘፈን አደረገ፡፡

20ኛው ኦሊምፒያድ የጀርመኗ ሙኒክ ከተማ በ1964 ዓ.ም (1972) ስታዘጋጅ የተካፈለችው ኢትዮጵያ ለወርቅ ባትታደልም በነሐስ ሜዳሊያ ለመታጀብ ችላለች፡፡ ማሞ ወልዴ በ40 ዓመት ዕድሜው ማራቶንን ሮጦ ሦስተኛ በመሆኑ፣ አንጋፋው የኦሊምፒክ ማራቶን ባለሜዳሊያ ተሰኝቷል፡፡

ከሙኒክ ስምንት ዓመት በኋላ በተደረገው የሞስኮ ኦሊምፒክ ሜዳሊያ ሠንጠረዥ ውስጥ ባትገባም ደረጀ ነዲ ሰባተኛ ሆኖ አጠናቋል፡፡ በባርሴሎና እና በአትላንታ ኦሊምፒኮች ውጤት የራቃት ኢትዮጵያ (በአትላንታ በሴቶች የፋጡማ ሮባ ድል ሳይዘነጋ)፣ የወርቅ ሜዳሊያን ያገኘችው ከ32 ዓመት ቆይታ በኋላ ነበር፡፡

በሲድኒ ኦሊምፒክ 27ኛው ኦሊምፒያድ በ1993 ዓ.ም (እ.ኤ.አ. 2000) ሲካሄድ  ገዛኸኝ አበራ ከስምንት ኦሊምፒያድ በኋላ ለኢትዮጵያ በማራቶን የወርቅ፣ ተስፋዬ ቶላ የነሐስ ሜዳሊያዎች ለማስገኘት ችለዋል፡፡ አንፀባራቂ ድልንም ተጎናፅፈዋል፡፡

ከሲድኒ በኋላ በተካሄዱት የአቴንስ፣ የቤጂንግና ለንደን ኦሊምፒኮች ኢትዮጵያ ከወርቁ ጋር ከተፋታች 16 ዓመታት ተቆጥረዋል (በለንደን የፀጋዬ ከበደ ነሐስ ሜዳሊያ ሳይዘነጋ)፡፡ ዘንድሮ ለኢትዮጵያ በወንዶች ማራቶን አምስተኛውን ወርቅ የሚያመጣውና አራተኛው ኢትዮጵያዊ የማራቶን ባለወርቅ የሚሆነው ኢትዮጵያዊ ማን ይሆን?

Standard (Image)

በግሎሪየስ ኩባንያ የታዳጊዎች ውድድር ከ100 በላይ ተተኪ ወጣቶች መምረጥ ተችሏል

$
0
0

-  33 ታዳጊ ወጣቶች በደደቢት እግር ኳስ ክለብ ተመርጠዋል

 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሚያደርገው የእግር ኳስ ጨዋታ ዝግጅት ሲጀምር፣ ተጫዋቾችን ሲመርጥ እንዲሁም ተጫውቶ ውጤት ከተመዘገበ በኋላ ከስፖርት ቤተሰቡ የሚሰነዘሩ አስተያየቶች ተደጋግሞ የሚሰጠው ‹‹በተተኪዎች ወይም በታዳጊዎች ላይ መሥራት አለበት›› የሚለው ነው፡፡

 

በስፖርት ፖሊሲው መሠረት በክልሎች እንዲሁም በከተማ አስተዳደሮች የታዳጊ ወጣቶች የእግር ኳስ ዓመታዊ ውድድሮች ሲደረጉ ቢታዩም፣ የተወሰኑት ሲሳኩ ቀሪዎቹ ደግሞ በማቴሪያል ወይም በአቅም ማነስ ሲያደርጉ ሲቀሩ ሲስተዋሉ ነበር፡፡

ለዚህም ሲባል ታዲያ አንዳንድ የግል ኩባንያዎች ወደ ስፖርቱ በመምጣት የተለያዩ ውድድሮችን እያከናወኑ ይገኛሉ፡፡

ከነሐሴ 1 እስከ 15 ቀን 2008 ዓ.ም. ድረስ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ፣ በግሎሪየስ ኩባንያና በአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አማካይነት ሲደረግ የሰነበተው የታዳጊ ወጣቶች እግር ኳስ ውድድር ነሐሴ 15 ቀን በአበበ ቢቂላ ፍጻሜ አግኝቷል፡፡ በሦስት አካላት ተተኪ ታዳጊዎችን ለማግኘት፣ የክረምት ጊዜያቸውን አልባሌ ቦታዎች ከማሳለፍ እንዲቆጠቡ እንዲሁም የእግር ኳስ ችሎታቸው እንዲገመገመው በማሰብ የተዘጋጀ ውድድር ነበር፡፡

በዚህ ውድድርም ከአሥሩም የአዲስ አበባ ክፍለ ከተማ የተውጣጡ ከ15 ዓመት በታችና ከ17 ዓመት በታች የሆኑትን ያሳተፈ ሲሆን፣ በድምሩ 440 ታዳጊ ወጣቶች ማወዳደር ተችሏል፡፡

ሁለት ሳምንት የቆየው የታዳጊዎቹ ውድድርም ከ104 በላይ የሚሆኑ ታዳጊዎች በክለብ ደረጃ ከወዲህ ሥልጠና እንዲያገኙ በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሚገኙ የእግር ኳስ ባለሙያዎች ዕድል ተመቻችቶላቸዋል፡፡

35 ታዳጊ ወጣቶችም በደደቢት እግር ኳስ ክለብ ሲመረጡ፣ ቀሪዎቹ ተጨማሪ ድጋፍና ሥልጠና እንዲሰጣቸው በተለያዩ ክለቦች ውስጥ እንደገቡ የግሎሪየስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ማርኬቲንግ ማናጀር ለአቶ ሙኒር አብዱልሀሚድ ሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ቀደም ብሎ ማኅበራዊ ግዴታ ለመወጣት በማሰብ በፈረስ ስፖርት ላይ ሲሳተፍ የነበረው ኩባንያው ዘንድሮ ደግሞ የእግር ኳስ ባለሙያዎች ባደረጉት ድጋፍ መሠረት ወደ ታዳጊ እግር ኳስ ተጫዋቾች ውድድሩን ለማድረግ እንደወሰኑ አቶ ሙኒር ገልጸዋል፡፡

በውድድሩም ላይ ታዳጊ ወጣቶቹ፣ አንድም ያላቸውን አቅም በመድረኩ እንዲያሳዩ፣ እንዲሁም የወደፊት የእግር ኳስ ገዛቸው እንዲያቁ ዕድል ይፈጥርላቸዋል በማለት አቶ ሙኒር አክለዋል፡፡

እንደ አቶ ሙኒር አስተያየት ከሆነ በሌሎች አገሮች የሚደረገው የታዳጊ ወጣቶች እግር ኳስ እንቅስቃሴ በኢትዮጵያም ውስጥ በሰፊው እንዲሠራ ባለሀብቶችን ወደ ዘርፉ በመግባት ቢሰማሩ የተሻለ ውጤት ማምጣት ይችላሉ፡፡

በሌላ በኩል የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት የሆኑት አቶ አማረ ማሞ በበኩላቸው ይህ በዓይነቱና በይዘቱ የመጀመሪያ የሆነ የታዳጊ ወጣቶች እግር ኳስ በቀጣይም ጠንክሮ እንደቀጠለ አስፈላጊውን ዕርዳታ ለማድረግ ፈቃደኛ እንደሆኑና የግሎሪየስ ኩባንያም ላደረገው ሙሉ የገንዘብ ድጋፍ አመስግነዋል፡፡

ግሎሪየስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ በአሁኑ ወቅት ስድስት የንግድ ምልክቶች ያላቸው ምርቶችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሕዝብ የሚያቀርብ ሲሆን በቀጣይም በሌሎች ስፖርቶች ለመሳተፍ ሁሉም እህት ኩባንያዎች ፈቃደኛ እንደሆኑ ተገልጿል፡፡

ለ15 ቀናት በቆየው በዚህ ውድድር ዓመት ከ15 በታች የአራዳ ክፍለ ከተማና ከ17 ዓመት በታች ውድድር የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የዋንጫ ተሸላሚ በመሆን አጠናቀዋል፡፡  

Standard (Image)

ኢትዮጵያ ያልተጠቀመችበት የኦሊምፒክ ስፖርት

$
0
0

በዓለም አቀፍ ደረጃ እ.ኤ.አ. 1966 ዓ.ም. ኢንተርናሽናል ቴኳንዶ አሶሴሽን ተብሎ ፌዴሬሽን እንደተቋቋመለት የሚገለጽለት ስፖርት በኢትዮጵያም በተለያዩ አካባቢዎች ሲዘወተር ቆይቷል፡፡

ሁለት አሥርት ዓመታትን በኢትዮጵያ ያሳለፈው ስፖርት በተለይ በዓለም አቀፉ የቴኳንዶ ፌዴሬሽኖች ስምምነት ለሦስት መከፋፈሉ ይታወሳል፡፡

በኢትዮጵያም የኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ቴኳንዶ፣ ኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ቴኳንዶ አሶሴሽን፣ ኢትዮጵያ ቴኳንዶ አሶሴሽንና ኢትዮጵያ ዩናይትድ ቴኳንዶ አሶሴሽን የሚል ስያሜ በማግኘት ተቀምጧል፡፡ ከነዚህም አሶሴሽኖች ኢትዮጵያ ዩናይትድ ቴኳንዶ አሶሴሽን አንጋፋው ያደርገዋል፡፡ አሶሴሽኑም በማስተር አብዲ ከድር መሪነት 26 ዓመታት የቆየ ሲሆን በ1997 ዓ.ም. ዕውቅና በማግኘት የተለያዩ ውድድሮችና ሥልጠና ሲያካሂድ ቆይቷል፡፡

ነሐሴ 13 እስከ 14 2008 ዓ.ም. አዲስ አበባ በሚገኘው ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ በተሰጠው የሙያ ማሻሻያ ሥልጠና ሁለቱን የከተማ አስተዳደሮችና ዘጠኙን ክልሎች በማሳተፍ ከአንድ ሺሕ በላይ ለሚሆኑ የቴኳንዶ ሠልጣኞችና አሠልጣኞች በአሶሴሽኑ ፕሬዚዳንት ማስተር አብዲ አማካይነት ሥልጠና ሲሰጥ ነበር፡፡

በቅርቡ ስምንተኛ ዳን ያገኙት ማስተር አብዲ ከአዲስ አበባ ብቻ ዕድሜያቸው ከ4 ዓመት ጀምሮ እስከ 13 የሚሆኑ 700 ሕፃናትን ከቴክኒካዊ እንቅስቃሴዎች ባሻገር በሥነ ልቦና ጋር በተያያዘ ሥልጠናዎችን ሰጥተዋል፡፡

ቀደም ባሉት ጊዜያት በጫካ ውስጥ ብቻ ይሰጥ የነበረው የቴኳንዶ ስፖርት፣ በአሁኑ ወቅት በመላ ኢትዮጵያ ከ30 ሺሕ በላይ ሠልጣኞች መኖራቸውን ማስተር አብዲ አብራርተዋል፡፡

በአሜሪካ፣ በጀርመን፣ ለንደንና ኦስትሪያ ተመሳሳይ ሥልጠና በመስጠትና ልምድ መቅሰም የቻሉት ማስተር አብዲ ስፖርቱ ላይ ከፍተኛ የሆነ የማስፋፋትን ሥራ በመሥራት ከጊዜ ወደ ጊዜ የተሳታፊዎች ቁጥር መጨመር እንደተቻለ ተናግረዋል፡፡

በቴኳንዶ ስፖርት 46 ዓመታት ያሳለፉት ማስተር አብዲ በአሁኑ ጊዜ በየክልሉ ቢያንስ ከ60 በላይ እውቅና የተሰጣቸው ክለቦች መኖራቸውንም አክለዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ 200 ክለቦች እንዳሉ የገለጹት ማስተር አብዲ ‹‹ቴኳንዶ ስፖርት ላይ ከማዘውተርና ለውድድር ከመቅረብ ባሻገር ሕፃናትና ታዳጊ ወጣቶችን በትምህርታቸውና በሥነ መግባር ታንጸው እንዲወጡ ይረዳቸዋል፤›› በማለት ይናገራሉ፡፡

የኢትዮጵያ ኢንተርናሽናል ቴኳንዶ ፌዴሬሽን የጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ከበደ እጅጉ በፌዴሬሽናቸው ሥር ያሉትን ሦስቱ አገር አቀፍ የቴኳንዶ አሶሴሽኖች በዓመታዊ ዕቅዳቸው ውስጥ ከሚያካትቷቸው ጉዳዮች ውስጥ የአቅም ግንባታ ወይም ለስፖርተኞች ሥልጠና መስጠት እንዲህም ከተለያዩ የዓለም አገሮች ጋር ግንኙነትን በመፍጠር ውድድር ማዘጋጀት እንደሆነ ያብራራሉ፡፡

እነዚህ ዕቅዶች ለማሳካት በየዓመቱ በቂ ደጋፍ እንደሚያደርግ የገለጹት ኃላፊው ‹‹ሦስቱም የቴኳንዶ አሶሴሽኖች ዓለም አቀፍ ግንኙነት በማጠናከር የተለያዩ ልምዶችን በማከፈልና በመቅሰምና ስፖርቱን በማሳደግ በኦሎምፒክ ደረጃ ተሳታፊ መሆን ይችላሉ፤›› በማለት ይገልጻሉ፡፡

በቀጣይ የኦሎምፒክ ውድድሩ ላይ ለመሳተፍ ፈቃድ እንዳገኘ የተናገሩት ማስተር አብዲ ለዝግጅት እንዲረዳም በ2009 ዓ.ም. በአገር ውስጥና ከአገር ውጭ ውድድሮች በማድረግ ከወዲህ ዝግጅት ለማድረግ እንዳሰቡ ተናግረዋል፡፡

ሦስቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ቴኳንዶን በማሠልጠን የሚታወቁት አሶሴሽኖች በተደጋጋሚ በፌዴሬሽን ደረጃ ለማደረጀት ጥያቄ ሲያነሱ ይስተዋላሉ፡፡ አቶ ከበደ ‹‹በሚኒስቴሩ ደንብ ላይ አገር አቀፍ የስፖርት ማኅበራት ሕግ በመኖሩ ያንን ሕግ አሟልተው መቅረብ ሲችሉ ጥያቄያቸው ሊስተናገድ ይችላል፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

በሚኒስቴር ደንቡ መሠረት አንድ ፌዴሬሽን በአምስት ክልሎች ላይ ስፖርቱን ማንቀሳቀስ ከቻለ የፌዴሬሽን አደረጃጀት ፍቃድ ማግኘት አለበት በሚል የኢትዮጵያ ቴኳንዶ አሶሴሽን ጥያቄ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡

Standard (Image)

የአትሌት ሌሊሳ ፈይሳ ጉዳይ ከነውዝግቡ ቀጥሏል

$
0
0

በሰላሳ አንደኛው የሪዮ ኦሊምፒክ ኢትዮጵያ አትሌቶቿን ከነሐሴ 6 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ስታሳትፍ ቆይታለች፡፡ ውድድር ለማድረግ ቀድመው ወደ ሥፍራው ያመሩት አትሌቶችን ጨምሮ በውድድሩ ፕሮግራም መሠረት በተለያዩ ቀናት አትሌቶቹ ወደ ሪዮ ማምራት ችለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከተሳተፈችባቸው ውድድሮች ውስጥ አትሌቲክስ፣ ብስክሌትና የውኃ ዋና ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በመጀመሪያው ቀን የሪዮ ኦሎምፒክ የአከፋፈት ሥነ ሥርዓት ላይ የኢትዮጵያ ባንዲራን ከያዘው አትሌት አነጋጋሪ ጉዳዮች ሲሰሙ ነበር፡፡ ይኸው አትሌት ሮቤል ኪሮስ ኢትዮጵያን ወክሎ ያመጣው ውጤትና ያሳው አቋም በውኃ ዋና የዓለምን ሚዲያ ቀለብ የገዛ እንደነበር ይታወሳል፡፡

ነሐሴ 15 ቀን 2008 ዓ.ም. ኢትዮጵያን በማራቶን በመወከል 2 ሰዓት ከ9 ደቂቃ ከ54 ሰከንድ ርቀቱን በመጨረስ የብር ሜዳለያ ያገኘው ፈይሳ ሌሊሳ ጉዳይ በመዝጊያውም ቀን የብዙ ታላላቅ ሚዲያዎችን ዳግም ቀልብ ገዝቷል፡፡ ሁለት እጆቹና በማጣመር በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በተለይ በኦሮሚያ ክልል እየተደረገ ያለውን የተቃውሞ እንቅስቃሴ በመደገፍ ያሳየው ምልክት ውዝግብ አስነስቷል፡፡ አትሌቱ ውድድሩን በማጠናቀቅ እንዲሁም ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት ተመሳሳይ ድርጊት ሲያደርግ ነበር፡፡ በጋዜጣዊ መግለጫ ወቅትም በጉዳዩ ላይ ከጋዜጠኞች በቀረበለት ጥያቄ መሠረት ‹‹ወደ አገር ቤት ከተመለስኩ ይገሉኛል ወይም ወደ ዘብጥያ ያወርደኛል፤›› ሲል ተናግሯል፡፡

አትሌት ሌሊሳ ፈይሳ በኦሊምፒክ ላይ እንደዚህ ዓይነት የፖለቲካ ጉዳይን በውድድር ላይ ማሳየቱ የብር ሜዳሊያውን ሊያስነጥቀው ይችላል የሚል የብዙዎች ስጋት ነበር፡፡ ነገር ግን የብር ሜዳሊያውን ከመነጠቅ ድኗል፡፡

በጉዳዩ ላይ የተለያየ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ትኩረት በመስጠት ሲዘግቡ ቀናት ተቆጥረዋል፡፡ የኢትዮጵያ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ በጉዳዩ ላይ ሐሳብ ሲሰጡ ተደምጠዋል፡፡

በዚህም መሠረት ‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት ለጀግና አትሌታችን ሌሊሳ ፈይሳ የጀግና አቀባበል ያደርግለታል፤›› በማለት አቶ ጌታቸው በፋና ብሮካስቲንግ ኮርፖሬት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ሲመጣ ምንም ዓይነት ችግር ሊያጋጥመውም እንደሚያችል ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ሲናገሩ ተሰምቷል፡፡

አትሌቱ ተቃውሞውን ካሰማ በኋላ ለተለያዩ አገሮች የጥገኝነት ጥያቄ እንደሚያቀርብ የተናገረ ሲሆን የገንዘብ መዋጮ በወጪ በሚገኙ የኢትዮጵያ ነዋሪዎች እየተደረገለት መሆኑን እየተገለጸ ይገኛል፡፡ በሪዮ ኦሊምፒክ ለመሳተፍ ወደ ብራዚል ያቀኑት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ነሐሴ 17 ቀን 2008 በኢትዮጵያ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አቀባበል ተደርጐላቸዋል፡፡

ኢትዮጵያ በውድድሩ አንድ የወርቅ፣ ሁለት የብርና አምስት የነሐስ በድምሩ 8 ሜዳልያዎች ማምጣቷ ይታወሳል፡፡  

በዚህ የሜዳሊያ ስብስብ ከ207 አገሮች 44ኛ ደረጃ የተቀመጠች ሲሆን ከአፍሪካ ሦስተኛ ደረጃ በመያዝ ማጠናቀቅ ችላለች፡፡

 

 

Standard (Image)

የገንዘቤ ዲባባ የዳይመንድ ሊግ ድሏ

$
0
0

የሪዮ ኦሊምፒክ በተጠናቀቀ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ የዘንድሮው ዳይመንድ ሊግ ሩውዝ (ሩጫ፣ ውርወራና ዝላይ) ውድድር፣ ባለፈው ሐሙስ (ነሐሴ 19 ቀን 2008 ዓ.ም.) በሎዛን (ስዊዘርላንድ) ቀጥሏል፡፡ ኢትዮጵያዊቷ ገንዘቤ ዲባባ በ3000 ሜትር ሩጫ በ8፡31.84 ደቂቃ በማሸነፍ የቦታውን ሪከርድ አስመዝግባለች፡፡ የሪዮ ኦሊምፒክ የ1500 ሜትር ብር ሜዳሊያ አሸናፊዋ ገንዘቤ፣ ውድድሩ ሊጠናቀቅ 400 ሜትር ሲቀር ተስፈንጥራ በመውጣት፣ ከስድስት ዓመት በፊት በኬንያዊቷ ቪቪያን ቼሩየት የተያዘውን ሪከርድ በሦስት ሰከንድ ግድም አሻሽላዋለች፡፡ የቅርብ ተቀናቃኟ የነበረችው በሪዮ በ5000 ሜትር ብር ሜዳሊያ ተሻሚዋ ኬንያዊቷ ሔለን ኦቢሪ ሁለተኛ፣ ሌላው ኬንያዊት ሜርሲ ቼሮም ሦስተኛ ሆነው ገብተዋል፡፡ እስከ ስድስተኛ ያለውን ቦታ ኬንያውያቱ ሲቆጣጠሩ ኢትዮጵያዊቷ ሀብታምነሽ ፈንታዬ 7ኛ ሆና ፈጽማለች፡፡ ገንዘቤ ባሰባሰበችው 10 ነጥብ ዳይመንድ ሊጉን ስትመራ ኦቢሪ በ6 ነጥብ በሁለተኛነት ትከተላለች፡፡ ዳይመንድ ሊጉ ነሐሴ 21 በፓሪስ የቀጠለ ሲሆን፣ የመጨረሻዎቹ 13ኛ እና 14ኛ ውድድሮች ሐሙስ ነሐሴ 26 እና ጳጉሜን 4 ቀን በዙሪክና በብራስልስ ከተሞች ከተካሄዱ በኋላ እ.ኤ.አ. የ2016 ዳይመንድ ሊግ ይጠናቀቃል፡፡

 

Standard (Image)

በሪዮ ኦሊምፒክ የተገኘውን ውጤት የተቹት ታዋቂ አትሌቶች አመራሮቹ እንዲነሱ ጠየቁ

$
0
0

ኢትዮጵያ በሪዮ ኦሊምፒክ ያስመዘገበችውን ደካማ ውጤት የተቹት የቀድሞ ታዋቂ አትሌቶች ብሔራዊ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ ለመፍትሔው በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ እንዲጠራ አሳሰቡ፡፡

በነባርና ታዋቂ አትሌቶች እንዲሁም ከቀድሞ አሠልጣኞች የተውጣጣው የአትሌቶች ጊዜያዊ ኮሚቴ ነሐሴ 19 ቀን 2008 ዓ.ም. በብሔራዊ ሆቴል ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡ ባለፈው ሳምንት በተጠናቀቀው የሪዮ ኦሊምፒክ ኢትዮጵያ ባስመዘገበችው ደካማ ውጤት ተጠያቂው ፌዴሬሽኑ ነው ብሏል፡፡

በ31ኛው አሊምፒያድ ተካፍሎ ከሪዮ በአንድ ወርቅ፣ ሁለት ብርና አምስት ነሐስ ሜዳሊያዎች የተመለሰው የኢትዮጵያ ቡድን ካለፉት ኦሊምፒኮች ያነሰ ውጤትና ደካማ እንቅስቃሴ አሳይቷል፡፡

‹‹የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በተገቢው መንገድ ሥራውን እየሠራ አይደለም፤ አትሌቲክሱ ወዳልተገባ መንገድ እያመራ ነው፤›› ያለው የጊዜያዊ ኮሚቴው ሰብሳቢ ኃይሌ ገብረሥላሴ፣ ኢትዮጵያ በሪዮ ኦሊምፒክ ያሳየችው ደካማ አቋም ፌዴሬሽኑ ወደ ሪዮ ከማምራቱ በፊት የተነሱትን ችግር ያለመፍታቱና የአመራሮች ኦሊምፒኩን በትኩረት ያለመመልከት ውጤት ነው ብሏል፡፡

‹‹የአመራረጥ፣ የልምምድ፣ የአሠልጣኞችና የአትሌቶች አመራረጥ ትኩረት ማጣት ከጊዜ ወደ ጊዜ የአትሌቲክሱ ውጤት ላይ ከፍተኛ ማሽቆልቆል እንዲመጣ አድርጓል፤›› ያለው ኃይሌ ገብረሥላሴ ‹‹አትሌቶቻችን ወደ ሪዮ ከመጓዛቸው በፊት ሥጋታችንን ብናስቀምጥም ሰሚ በማጣታችን የፈራነው ነገር ደርሷል፡፡ ከዚህ በኋላ ግን ወደ ኋላ ሳይሆን ወደፊት መሄድ ይገባናል፤›› ብሏል፡፡

ኮሚቴው በመፍትሔነት ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ጠቅላላ ጉባኤ ጠርቶ አመራሮቹ እንዲነሱና ባለሙያዎች እንዲተኳቸው ጥሪ አቅርቧል፡፡ ከየክልሉ የሚወከሉም ሆነ ፌዴሬሽኑን የሚመሩት በአትሌቲክስ ውስጥ ያለፉና አትሌቲክሱን የሚያውቁ መሆን እንዳለበት ኮሚቴው ገልጿል፡፡  

በጋዜጣዊ መግለጫው የሲድኒ ኦሊምፒክ የማራቶን ወርቅ ባለቤት የነበረው ገዛኸኝ አበራ ‹‹እኛ ቤቱን ለመገንባት እንጂ ለማፍረስ አልተነሳንም፣ ይልቁንም ከ16 ዓመት በፊት አራት ወርቅ አምጥተን ዛሬ ላይ ለምን አንድ ወርቅ ብቻ እናመጣለን?›› በማለት ጠይቋል፡፡ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2000 በተካሄደው የሲድኒ ኦሊምፒክ በኦሊምፒክ ታሪኳ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበችበት ነበር፡፡ ያኔ 4 ወርቅ 1 ብር 3 ነሐስ በድምሩ 8 ሜዳለያዎች አግኝታ ነበር፡፡  

ገዛኸኝ ‹‹አትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ ከቀድሞ ባለሙያዎች ጋር ተቀራርቦ ካልሠራና በአመራር ቦታ ላይ የተሰየሙትን አካላት በአትሌቲክስ ውስጥ ባለፉ ካልተካ ከዛሬ የባሰ እንጂ የተሻለ ውጤት ይመጣል ማለት ይከብዳል፤›› ብሎም ሥጋቱን አስቀምጧል፡፡

በተለይ በሥልጠና ወቅት አትሌቶቹ በግላቸው በመሥራትና ቀደም ብሎ በአሠልጣኝ ዶ/ር ወልደ መስቀል ኮስትሬ ይሰጥ የነበረውን የልምምድ መንገድ ወደ ጎን በማድረግ በተቃራኒው አትሌቶቹ በራሳቸው መንገድ አሠልጣኞቻቸውን የሚያዙበት ጊዜ ሆኗል ያሉት ኮማንደር አበበ መኮንን ናቸው፡፡

ከቀድሞው ዋና አሠልጣኝ ዶ/ር ወልደ መስቀል ኮስትሬ ጋር ማሠልጠን የቻሉት ኮማንደር አበበ፣ ‹‹ሥልጠናው ችግር አለበት፡፡ የትኛውም ዓለም የአትሌቲክስ ሥልጠና በቡድን እንጂ በግል አይደለም፡፡ ሥልጠናው በባለሙያዎች ጭምር እንጂ በትምህርት ብቻ ሊከናወን አይቻልም፤›› ብለዋል፡፡

አንጋፋዎቹ አትሌቶች ጋዜጣዊ መግለጫቸውን ያጠቃለሉት፣ አትሌቲክሱን የሚመራው አካል ቀና ምላሽ ካልሰጠና ከውሳኔ ላይ ካልደረሰ መሄድ ያለበት ርቀት ድረስ እንደሚሄድ መዘጋጀታቸውን አስጠንቅቀዋል፡፡ መፍትሔ ለማፈላለግም ወደ ዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር ላይ እንደሚያነጣጠሩም ተመልክቷል፡፡

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ቡድን አዲስ አበባ እንደደረሰ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ኢንጂነር መሰለ፣ የተገኘው ውጤት የሚያበረታታ ነው ብለዋል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ በኦሊምፒኩ ደካማ ሆና ሳይሆን የሌሎች ጠንካራ መሆን ነው፤›› ሲሉም ተደምጠዋል፡፡ ለመጣውም ውጤት ‹‹ምንም ዓይነት ይቅርታ›› ፌዴሬሽኑ እንደማይጠይቅና ወደፊት በጉዳዩ ላይ አስፈላጊው ማብራሪያ እንደሚሰጥ አስታውቀዋል፡፡

ኢትዮጵያ በሪዮ ኦሊምፒክ የሰበሰበቻቸው 8 ሜዳሊያዎች ያገኙት አልማዝ አያና (ወርቅ 10,000 ሜትር እና ነሐስ 5,000 ሜትር)፣ ጥሩነሽ ዲባባ (ነሐስ 10,000 ሜትር)፣ ታምራት ቶላ (ነሐስ 10,000 ሜትር)፣ ገንዘቤ ዲባባ (ብር 1,500 ሜትር)፣ ሐጎስ ገብረሕይወት (ነሐስ 5,000 ሜትር)፣ ማሬ ዲባባ (ነሐስ ማራቶን) እና ፈይሳ ሌሊሳ (ብር ማራቶን) መሆናቸው ይታወሳል፡፡

 

Standard (Image)

እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከትጥቅ አምራቹ ኤሪ ጋር የ90 ሺሕ ዩሮ ስምምነት ተፈራረመ

$
0
0

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን  ከትጥቅ አምራቹ ኤሪ ጋር ለአራት ዓመት የሚቆየውን ስምምነት በጣሊያን ባህል ማዕከል ነሐሴ 24 ቀን 2008 ዓ.ም. ተፈራረመ፡፡ በሁለቱም ፆታ ከ17 ዓመት እስከ ዋና ብሔራዊ ቡድን አገልግሎት የሚውል በየዓመቱ ከትጥቅ አምራቹ የ90 ሺሕ ዩሮ የሚገመት ትጥቅ ያገኛል ተብሏል፡፡ ወደ አገር ውስጥ ከሚገቡት ትጥቆችም ከቀረጥ በስተቀር ሙሉ ወጪውን የትጥቅ አምራቾች ድርጅት ኤሪ የሚሸፈነው ይሆናል፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንም ተጨማሪ ትጥቅ መግዛት ሲፈልግ በ20 በመቶ ቅናሽ ተደርጎለት በ50 ሺሕ ዩሮ መግዛት እንደሚችል በስምምነት ወቅት ተብራርቷል፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የፊታችን ቅዳሜ  ከሲሰልሽ አቻው ጋር በሐዋሳ ስታዲየም በሚያደርገው የማጣሪያ ጨዋታ በአዲስ መለያ እንደሚጫወት የፌዴሬሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አስታውቀዋል፡፡

 በዳዊት ቶሎሳ

Standard (Image)

ኦሊምፒክ ኮሚቴው በሪዮ ለተመዘገበው ውጤት ኃላፊነቱን እንደሚወስድ ገለጸ

$
0
0

በዳዊት ቶሎሳ

በሪዮ ኦሊምፒክ ኢትዮጵያ ባገኘችው ውጤት ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው ቅር እንደተሰኘ ገልፆ፣ ለውጤቱም ተጠያቂ የሚያደርገው አካል ካለ ቅጣቱን መቀበል እንደሚችል ማክሰኞ ነሐሴ 24 ቀን 2008 ዓ.ም. በጠራው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አስታውቋል፡፡

የብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ከፍተኛ አመራሮች ባልተገኙበት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ በውድድሩ ላይ በኢትዮጵያ አትሌቶች ላይ ከፍተኛ የሥልጠና ችግር እንደተስተዋለባቸውና በቡድን ያለመሥራታቸው የታሰበው የወርቅ ሜዳሊያ መምጣት እንዳልተቻለ አቶ ታምራት በቀለ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ዋና ዳይሬክተርና የሪዮ ኦሊምፒክ ቡድን መሪ አብራርተዋል፡፡

እንደ አቶ ታምራት ገለጻ ከሆነ አትሌቶች ቀደም ብለው አቅም ባለው ባለሙያ አለመሥራታቸው በሥነ ልቦና፣ በምግብ እንዲሁም በቅንጅት አለመሥራታቸው በኦሊምፒክ ኮሚቴው ተገምግሟል፡፡

ኦሊምፒክ ኮሚቴ ቀደም ብሎ ያቀደውን አራት የወርቅ፣ አራት የብርና አራት የነሐስ ሜዳሊያ አለማሳካቱ፣ ተከታታይ የሆነ ሥልጠና ያለመሰጠቱን እንደምክንያትነት አንስቶ ‹‹በውጤቱ አዝነናል፤ ለዚህም ለሚጠይቀን አካል ቅጣቱን ለመቀበል ዝግጁ ነን፤›› በማለት የተናገሩት አቶ ታምራት፣ ‹‹በኦሊምፒኩ መድረክ 66 በመቶ ዕቅዳችንን ማሳካት ችለናል፤›› ብለዋል፡፡

በ31ኛው ኦሊምፒያድ ኢትዮጵያ ለማግኘት ካቀደችው 12 ሜዳሊያዎች ውስጥ ስምንቱን 1 የወርቅ፣ 2 የብር እና 5 የነሐስ ሜዳሊያዎች ማግኘቷን የገለጹት ዳይሬክተሩ ከወርቅ አንፃር ግን አነስተኛ መሆኑን ሳይናገሩ አላለፉም፡፡

ከሁለት አሠርታት ወዲህ ኢትዮጵያ ከተካፈለችባቸው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በዘንድሮው የሪዮ ኦሊምፒክ የተመዘገበው ውጤት ዝቅተኛ የሆነው የአትሌቶች የቡድን ሥራ አለመኖርና የሥነ ልቦና ችግር መፈጠሩ እንደሆነ አቶ ታምራት ተናግረዋል፡፡ በቀጣዩ የቶኪዮ ኦሊምፒክ በተጨማሪ ስፖርቶች በኢላማ ተኩስና በጁዶ ስፖርት ለመሳተፍ ዕቅድ እንዳለም ሳይናገሩ አላለፉም፡፡

በዋና አሠልጣኝነት ወደ ሪዮ እንዲሄድ ስሙ ተላልፎ የነበረው አበበ ቢቂላ እንዲቀር የተደረገው በብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው ነው በማለት የውኃ ስፖርቶች ፌዴሬሽን ነሐሴ 23 ቀን 2008 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫ አስታውቆ ነበር፡፡ ኦሊምፒክ ኮሚቴው በበኩሉ በሰጠው ምላሽ ፌዴሬሽኑ የላከለትን ሁለት አትሌቶችና አንድ የቡድን መሪ ወደ ሪዮ እንዲያመሩ ማድረጉን አስታውሷል፡፡

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በበኩሉ በሪዮ ኦሊምፒክ የተመዘገበው ውጤት መልካም ነው ብሏል፡፡ በተለይ ረዥም ርቀቱን በተመለከተ አሠልጣኝ ሁሴን ሼቦ በሰጡት አስተያየት ‹‹በታሪክ ሊተላለፍ የሚችል የቡድን እንቅስቃሴ ማሳየት ችለናል›› በማለት ቅዳሜ ነሐሴ 21 ቀን 2008 ዓ.ም. በወቅታዊ ጉዳይ ላይ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አብራርተዋል፡፡

 

Standard (Image)

አትሌቲክሱ በባለሙያዎች እንዲመራ ለማድረግ ከክልሎች ጋር እንደሚመክሩ አትሌቶች አስታወቁ

$
0
0

ለብሔራዊ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አመራርነት የሚወክሏቸው በስፖርቱ ያለፉ እንዲሆኑ ለማድረግ ከክልሎች ጋር እንደሚመክሩ የአትሌቶች ማኅበርና ጊዜያዊ የአትሌቶች ኮሚቴ አስታወቁ፡፡

በስለሺ ስህን የሚመራው የኢትዮጵያ አትሌቶች ማኅበርና በኃይሌ ገብረሥላሴ የሚመራው ጊዜያዊ የአትሌቶች ኮሚቴ በወቅታዊው የአትሌቲክስ ጉዳይ ላይ ነሐሴ 27 ቀን 2008 ዓ.ም. በብርሃኔ አደሬ አፍሪካ ሞል በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በሪዮ ኦሊምፒክ ውጤት መጥፋት አንዱ ምክንያት የቡድን ሥራ ክፍተት የታየው ሲንከባለል የመጣው የፌዴሬሽኑ ችግር መሆኑን፣ የአትሌቶች ጊዜያዊ ኮሚቴ ሰብሳቢ ኃይሌ ገብረሥላሴ ተናግሯል፡፡ እንዲሁም ‹‹ሕጋዊ ይሁን አይሁን ዓላማችን አትሌቲክሱን ማዳን ነው! የምናረጋግጥላችሁ ወደ ኋላ እንደማናፈገፍግ ነው፤›› በማለት አስታውቋል፡፡

ማኅበሩና ጊዜያዊው ኮሚቴ እንዴት አንድ ላይ ቆሙ? ለሚለው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ‹‹ሁለቱም የቆሙት ለአትሌቶችና ለአትሌቲክሱ ነው፡፡ አትሌክስ በስፖርቱ ውስጥ ባለፈ መመራት ስላለበት፡፡ ክልሎች ይህንኑ እንዲፈጽሙ እንመክራለን፤›› ብለዋል፡፡

የአትሌቶች ጊዜያዊ ኮሚቴ፣ ለተፈጠረው ችግር ፌዴሬሽኑ አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲጠራ ለሰጠው ማሳሰቢያ አሉታዊ ምላሽ የሰጠው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ከጉዳዩ ጋር የማይያያዝ ‹‹አትሌቶች መኪና ከቀረጥ ነጻ ያስገባሉ›› ብሎ መናገሩ ተገቢ እንዳልሆነ በመግለጫው ተመልክቷል፡፡ የጊዜያዊው ኮሚቴ ሰብሳቢው ኃይሌ ገብረሥላሴ ‹‹መንግሥት ኃይሌ ወይም ሌላ ስለሆነ ከሕግ ውጭ ሥራ አይሠራም›› በማለት ምላሽ ሰጥቷል፡፡ አያይዞም ‹‹የስፖርቱ ባለቤት እኛ መሆናችንን ማመን አለባቸው፡፡ አሁን አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ላይ ነን፡፡ ከዚያ ወደ ኦሊምፒክ ኮሚቴ እንመጣለን፤›› ብሏል፡፡

‹‹ስለ ሪዮ ውጤት ጠይቀናቸው ስለመኪና ታክስ የማይገናኝ ነገር ያነሱብናል፤›› ያሉት ደግሞ የቀድሞ ኦሊምፒያንና ታዋቂው አሠልጣኝ ቶሎሳ ቆቱ ናቸው፡፡ እንደሳቸው አነጋገር የፌዴሬሽኑ መሠረታዊ ችግር ባለሙያ ያለመቀመጡ እንደሆነ በምሳሌያዊ አነጋገር ‹‹ከበሮ በማያውቁት ሰው ሲመታ ነው ችግሩ›› በማለት ተናግረዋል፡፡ አትሌቶችና አሠልጣኞች መቼም እንደማይነጣጠሉ ያመለከቱትም በፌዴሬሽኑ ውስጥ የአንበሳውን ድርሻ መያዝ ያለባቸው አትሌቶች ናቸው በማለትም ነው፡፡

 

Standard (Image)

‹‹ሕጉ የግድ በባለሙያ ለመመራት ሲድኒ ላይ የሮጠ ብቻ በአመራር ይቀመጥ አይልም››

$
0
0

አቶ አምበሳው እንየው፣ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ

በቅርቡ በተጠናቀቀው የሪዮ ኦሊምፒክ ኢትዮጵያ ያስመዘገበችውን ዝቅተኛ ውጤት በተመለከተ በተለያዩ ወገኖች ከተርታው ኅብረተሰብ እስከ ታዋቂ ወርቃማ አትሌቶች በቁጭት ሲናገሩ ተሰምቷል፡፡ ብሔራዊ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንና ኦሊምፒክ ኮሚቴ ያቀዱት አራት ወርቅ፣ አራት ብርና አራት ነሐስ ውኃ የበላው መጀመሪያውኑ የእቅድ ምሰሶው መሠረት የሌለው በመሆኑ ነውም ብለውታል፡፡ የቀድሞ ታዋቂ አትሌቶችንና አሠልጣኞችን ያቀፈውና በኃይሌ ገብረሥላሴ የሚመራው ጊዜያዊ ኮሚቴ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በአስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ እንዲበተን ጥሪ አቅርበውበታል፡፡ የኦሊምፒክ ቡድኑ በ31ኛው ኦሊምፒያድ ይዞ የተመለሰው አንድ ወርቅ ሁለት ብርና አምስት ነሐስ የስኬት መገለጫ ነው በማለት ብሔራዊ ፌዴሬሸኑም ሆነ ኦሊምፒክ ኮሚቴው አወድሰውታል፡፡ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴርም የሁለቱን ተቋማት አስተያየት ይጋራል፡፡ እንዲያውም በነሐስ ሜዳሊያዎች ብዛት ካለፉት ኦሊምፒኮች ሲታይ በሪዮ የተሻለ ውጤት ማምጣት ተችሏል፣ በወርቅ ዝቅተኛ ቢሆንም በኦሊምፒክ በራሱ መሳተፍ በጎ ጎን ነው በማለት ሚኒስትር ዴኤታው አቶ አምበሳ እንየው በጽሕፈት ቤታቸው ነሐሴ 25 ቀን 2008 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል፡፡ በኃይሌ ገብረሥላሴ የሚመራውን ጊዜያዊውን የአትሌቶች ኮሚቴ ‹‹አናውቀውም›› በማለት ተናግረዋል፡፡ ከጋዜጠኞች ለተነሳላቸው ጥያቄዎች የሰጡትን ምላሽ ዳዊት ቶሎሳአቀናብሮታል፡፡

ጥያቄ፡- ኢትዮጵያ በ31ኛው ኦሊምፒያድ በአትሌቲክሱ ያሳየችው ውጤት ዝቅተኛ መሆኑ ታምኗል፡፡ በአንፃሩ ደግሞ ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ ጨዋታዎች መሳተፏ እንደ መልካም ጎን መወሰድ አለበት እንጂ ውጤቱን በሜዳሊያ ብቻ መመዘን አይቻልም ሲባል ምን ለማለት ተፈልጎ ነው?

አቶ አምበሳው፡-ቀደም ብሎ በሪዮ ኦሊምፒክ አራት ወርቅ አራት ብርና አራት ነሐስ ለማምጣት ታቅዶ ነበር፡፡ በነሐስ ካለፉት ኦሊምፒያዶች ሲታይ በሪዮ የተሻለ ውጤት ማምጣት ተችሏል፡፡ በወርቅ ግን ዝቅተኛ የሚባል ውጤት ነው ያስመዘገብነው፡፡ በአንጻሩ ግን በኦሊምፒኩ መሳተፋችን ራሱ እንደ በጎ ጎን መታሰብ አለበት፡፡ ምክንያቱም በዝግጅት ወቅት የታሰበው የወርቅ መጠን ‹‹ጅምላ ዕቅድ›› ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ለዚህም ደግሞ በአትሌቲክሱ የታቀደው የሜዳሊያ መጠን ጥልቅ ጥናት ሳይደረግበት ነው፡፡ በ5,000 እና 10,000 ላይ ወርቅ ያመጣሉ ተብለው የታሰቡት አትሌቶች በሥልጠና ወቅት ከብሔራዊ ቡድን ውጪ ነበሩ፡፡ በኦሊምፒክ ላይ አንድ ወርቅ ስለመጣ ብቻ አትሌቲክሱ አሽቆልቁሏል ማለት አይቻልም፡፡ ኢትዮጵያ በቀደምቱ ኦሊምፒኮች ከተሳተፈችበት መድረኮች ጋር ለማነፃፀር ያክል ለምሳሌ ከባርሴሎና፣ ሜክሲኮ፣ ቶኪዮና ሮም እንዲሁም ሙኒክ ከነበረው በሪዮ ያመጣነው ነሐስ ሜዳሊያ ቁጥር የተሻለ ነው፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ በኦሊምፒኩ ታሪክ ካልተሳተፈችበት የሲኦል፣ ሎሳንጀለስ እንዲሁም ሞንትሪያል ኦሊምፒኮች በሪዮ ኦሊምፒክ ብዙ ክፍተቶች ቢኖርብንም በመድረኩ ላይ መሳተፍ መቻሏና አንድ ወርቅ ብቻ ስላመጣች በሜዳሊያ መጠን ብቻ መመዘን ያለባት አይመስለኝም፡፡ ይልቁንም በጥቂት ስፖርት ዓይነቶች በመሳተፍ ይህን ስምንት ሜዳሊያ ማስገኘቷ ትልቅ ነገር ነው፡፡

ጥያቄ፡- ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ መሳተፍ ከጀመረችበት ጊዜ ጀምሮ በተለይ በረዥም ርቀቱ ያመጣቻቸው ውጤቶች ጥሩ ነበር፡፡ አሁን ያለው የስፖርት ፖሊስ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል እየተባለ ውጤታማ አለመሆኗ በሦስት ስፖርቶች ብቻ ተካፍላ በተሳትፎ ጥሩ ደረጃ ላይ ነች የተባለው ከምን አንፃር ነው?

አቶ አምበሳው፡-ኢትዮጵያ መሳተፍ ከጀመረች ጀምሮ ከተካሄዱት 16 ኦሊምፒያዶች በ13ቱ መሳተፍ ችላለች፡፡ በፖለቲካ አለመመቻቸት ያልተሳተፈችባቸው ኦሊምፒኮች የሚያስቆጭ ጊዜ አድርገን እንወስደዋለን፡፡ አሁን የምንገኝበት ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳይ ከፍ ያለ ሆኖ እንዴት ውጤቱ ዝቅተኛ ይሆናል? ለሚለው የስፖርት ዕድገታችን በወርቅ ሊለካ አይችልም እንላለን፡፡ ግን ደግሞ እንደ ኦሊምፒክ ከተሳትፎ ቀጥሎ የሚመጣው ሜዳሊያ ሠንጠረዥ ውስጥ መግባት ነው፡፡ በሪዮ እናመጣዋለን ያልነውን ወርቅ ዝቅተኛ እንደሆነ እንቀበላለን፡፡ በአንፃሩ በስፖርት ኢንቨስትመንት ስንለካ በተሳትፎ፣ በቁሳቁስ ካለፉት ጊዜያት ደህና ሆነን ሻል ያለ ወርቅ ለምን አልመጣም? በሥልጠና ክፍተት ምክንያት ነው፡፡ ሌላው ተሳትፎ ሲባል በብዙ ስፖርቶች መሳተፍ ስንችል ነው የተባለው እውነት ነው፡፡ በሁሉም ስፖርት መሳተፍ አለመቻላችን እውነት ነው፡፡ ግን ደግሞ ከነበረን ተሳትፎ አድገናል፡፡ ድሮ የምንሳተፍበት ማራቶን፣ አሥር ሺሕ፣ ግፋ ቢል አምስት ሺሕ ነበር፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ስፖርትን ለማስተዋወቅ መንግሥት አይሠራም፡፡ ስፖርትን ማስተዋወቅ የስፖርት ፌዴሬሽን ሥራ ነው፡፡ መንግሥት ድጋፍ ብቻ ነው የሚያደርገው፡፡ ለምን በተለያዩ ስፖርት ዓይነቶች አልተሳተፍንም ስፖርቱ ስላልሰፋ ማሳተፍ አንችልም፡፡ ባልተስፋፋ ስፖርት ላይ መንግሥት ጊዜውን ማቃጠል አይፈልግም፣ የተስፋፉትን ከመደገፍ ውጪ፡፡

ጥያቄ፡- በሪዮ ለተመዘገበው ዝቅተኛ ውጤት መምጣት ክፍተቶቹ ምን ነበሩ?

አቶ አምበሳው፡-በሪዮ ኦሊምፒክ ለመጣው ውጤት የተለያዩ ችግሮች እንደነበሩ ሚኒስቴሩ የታዩትን ክፍተቶች ገምግሟል፡፡ በዚህም መሠረት የሥልጠና፣ የሥነ ልቦና፣ የቡድን ሥራ፣ የአመጋገብ ሥርዓት፣ አትሌቶቹን በማቀናጀት ሥራ ላይ ፌዴሬሽኑ ያሳየው ደካማ አቋም፣ እንዲሁም ኦሊምፒክ ኮሚቴው ቡድኑን መከታተልና መቆጣጠር ላይ ኃላፊነቱን እንዳልተወጣ መገምገም ችለናል፡፡ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑም የተለያዩ ችግሮች እንዳሉበት ተገልጿል፡፡ የመልካም አስተዳደር፣ የኪራይ ሰብሳቢነት ችግሮች እንዳለበት ፌዴሬሽኑም አስታውቋል፡፡ በቀጣይ በአሠራር፣ በተጠያቂነት የሚፈቱ ይሆናሉ፡፡

ጥያቄ፡- ከመልካም አስተዳደር ጋር በተያያዘ የውኃ ስፖርቶች ፌዴሬሽን ብቁ ሆኖ ስላልተገኘ ምንም ዓይነት ድጋፍ እንደማይደረግለት ተገልጿል፡፡ ድጋፍ እንዳይደረግለት የተወሰነበት ምክንያት ምንድነው? እንዲሁም በአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑም ተመሳሳይ ችግር ታይቶ ውሳኔ ያልተሰጠበት ምክንያት እንዴት ነው?

አቶ አምበሳው፡-የውኃ ስፖርቶች ፌዴሬሽን በተመለከተ ከሪዮ በፊት የተለያዩ ግምገማዎችን አድርገናል፡፡ ከውድድር በፊትም ተነጋግረናል፣ እርምት ወስደናል፡፡ ግን ሊቀበሉን አልቻሉም፡፡ ከዛ በፊት ከአሠልጣኞች የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ሲቀርቡልን ነበር፡፡ እንዲያስተካክሉ ነግረናቸዋል፡፡ ከሪዮ መልስም ስለተፈጠሩ ጉዳዮች ዝርዝር መረጃና ማስረጃ እንዲያቀርቡ ጠይቀናቸዋል፡፡ የምንጠይቃቸውን ጥያቄ አለመመለስ ብቻ አይደለም፡፡ አያገባችሁም የማለት ደረጃም ደርሰዋል፡፡ ስለዚህም በማያገባን ነገር ላይ ድጋፍ የምናደርግበት ምክንያት የለም፡፡ በአጠቃላይ ግን በአስተዳደር፣ በሥልጠና፣ በአመራር በመሳሰሉ ጉዳዮች ድጋፎቻችን እንድናቆም ተገደናል፡፡ ፌዴሬሽኑ ያሉበትን ችግሮች በተለይ ከመልካም አስተዳደር፣ ከሥልጠና እንዲሁም በተመሳሳይ ሁኔታዎች ላይ በቀጣይ እንደሚያርም ገልጿል፡፡ በእኛ በኩል ጠቅላላ ጉባኤ ላይ በአግባቡ ተቀምጦ እንዲያስተካክል ቁጥጥርና ክትትል እናደርጋለን፡፡ በዛ መንገድም ችግሮቻቸውን እንደሚፈቱ ገልጸዋል፡፡

ጥያቄ፡- አትሌቲክሱ በትክክለኛ መንገድ ላይ እየተጓዘ ነው ማለት ይቻላል?

አቶ አምበሳው፡-በእኛ እምነት አትሌቲክሱ ትክክለኛ መንገድ ላይ ነው፡፡ አትሌቲክሱ እያደገ ነው፡፡ አትሌቲክሱ እየበዛ ነው፣ የአገር ውስጥ ውድድሮችም እየበዙ ነው፡፡ አትሌቶችም በኢኮኖሚ አንፃር ቤተሰቦቻቸውም ጭምር እየተጠቀሙ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ግን ፌዴሬሽኑ ላይ ችግሮች አሉ፡፡ እነሱም በሒደት ይፈታሉ፡፡ በሕግ የሚነሱ ግድፈቶችን ከመፍታት ውጪ በአትሌቲክሱ ፌዴሬሽኑ ላይ ምንም አቋም የለንም፡፡

ጥያቄ፡- የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ቡድን ወደ ሪዮ ከማምራቱ በፊት እንዲሁም ከኦሊምፒኩም መልስ የቀድሞ አትሌቶች ጊዜያዊ ኮሚቴ በማቋቋም በአትሌቲክሱ ዙሪያ ጥያቄ ማንሳት ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡ በዚህ ጉዳይ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር ምን ይላል?

አቶ አምበሳው፡-የአትሌቶች ጊዜያዊ ኮሚቴ የሚባለውን አናውቀውም፡፡ ስለዚህ በማናውቀው ነገር ምንድነው ብለን በየቤቱ ዞረን መጠየቅ የለብንም፡፡ ጊዜያዊ ኮሚቴ መሆኑን፣ በማን እንደተጀመረና የምናውቀው መረጃና ዕውቅና የለም፡፡ እኛ እንደመንግሥት የምናውቀው የስፖርት ማኅበር የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን፣ እንዲሁም ደግሞ የሙያ ማኅበር የኢትዮጵያ አትሌቲክስ የአትሌቶች ማኅበርን ነው፡፡

ጥያቄ፡- የስፖርት ፌዴሬሽኖች በባለሙያ መመራት አለባቸው የሚለው አስተያየት ከተለያዩ ግለሰቦች ጥያቄ እያስነሳ ነው?

አቶ አምበሳው፡-በስፖርት ፌዴሬሽኖች ላይ የተሻሉ ሰዎች ወይም በስፖርት ውስጥ ያለፉ የሆኑ የሚለው አስተያየት ጥሩ ሐሳብ ነው፡፡ የተማረ ሰው ሀብት ያለው እንዲሆን፣ ከዘርፉ ጋር ግንኙነት ያለው እንዲሆን እንጂ አትሌት ያልነበረ መግባት የለበትም ብሎ መገደብ አይቻልም፡፡ ለዚህም የአምበሳውን ድርሻ ክልሎች ይወስዳሉ፡፡ የፈለጉትን መርጠው መላክ፣ የመረጡትን ማቅረብ ይችላሉ፡፡ ሌላው የአገሪቱን ሥርዓተ ትምህርት ባንቀወም ጥሩ ነው፡፡ በስፖርት ሳይንስ ውስጥ ያለፉ ሞያተኞች ከተለያዩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ይወጣሉ፡፡ ስለዚህ በዚህ ዘርፍም የሚመጡትም ከእነዚህም ባሻገር ደግሞ በዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ማኅበር ሥልጠና ወስደው የመጡትን እንደ ሞያተኛ መቀበል ያስፈልጋል፡፡ ሕጉ የግድ በባለሙያ ለመመራት ሲድኒ ላይ የሮጠ ብቻ በአመራር ይቀመጥ አይልም፡፡

ጥያቄ፡- ከመልካም አስተዳደር ጋር በተያያዘ በተለይ ከውኃ ስፖርት ጋር የሚነሱ ችግሮች ነበሩ፡፡ አንድ የፌዴሬሽን አመራር ከቦታው ከተነሳ በኋላ ወደ ሌላ ስፖርት ፌዴሬሽን ተመልሶ ሲሠራ በብዙዎች ቅሬታ ሲያስነሳ ይስተዋላል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ያለው አካሄድ ምን ይመስላል?

አቶ አምበሳው፡-በተለያዩ ጊዜያት የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች እንዲመለሱ ይደረጋል፡፡ ስለዚህ ውኃ ስፖርት ላይ የነበረው ልጅ በፊት የነበረበት ቦታ ላይ ባለመስማማቱ ከዛ ተነስቶ ሌላ ቦታ እንዲቀመጥ ተደርጓል፡፡ በዚህም መሠረት ፌዴሬሽኑ እንደ አትሌቲክስና እግር ኳስ መቅጠር ስለማይችል፣ እኛ አወዳድረን በሲቪል ሰርቪስ ሕግ መሠረት የትምህርት ደረጃቸውንና አገልግሎታቸው አይተን እንመድባለን፡፡ መዋቅር ሲሠራ አንዱን ከአንዱ ወስደን የምናሸጋግረው ነገር ይኖራል፡፡ በአጠቃላይ ግን የሚቀመጡት ሰዎች በትምህርት ደረጃቸው እንዲቀመጡ መደረግ አለበት፡፡

ጥያቄ፡- መንግሥት ለሪዮ ኦሊምፒክ ያደረገው የገንዘብ ድጋፍ ከፍተኛ ነው ማለት ይቻላል ወይ? ከኦሊምፒክ ኢትዮጵያ ምን ተጠቀመች?

አቶ አምበሳው፡-መንግሥት በሪዮ ኦሊምፒክ የሰጠው የገንዘብ ድጋፍ ከሌሎቹ ኦሊምፒኮች ትልቅ ነው፡፡ ያስፈቀድነውን ገንዘብ ግን ሙሉ በሙሉ አልተሰጠንም፡፡ አዎን መጠኑን መግለጽ ባያስፈልግም፡፡ ድሮ አራትና አምስት ሚሊዮን ብር ነበር የሚፈቅድልን፡፡ አሁን ግን ለኦሊምፒክ ብቻ ሳይሆን ለተለያዩ ውድድሮች ጭምር የተሻለ በጀት ሰጥቶናል፡፡ በኦሊምፒኩ ኮሚቴ በኩል ምን ያህል አገኙ? ምን ያህል ተጠቀሙ የሚያውቀው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ነው፡፡ በእኛ በኩልም በፊት ከሚሰጠው በጣም የራቀ ባይሆንም የገንዘብ ድጋፍ አድርገናል፡፡

ጥያቄ፡- አትሌቶች ለሪዮ ሲዘጋጁ ካለፉት ውድድሮች በተሻለ መጠን ይዘጋጁ እንደነበር አሠልጣኞቹም ጭምር ሲገልጹ ነበር፡፡ ሚኒስቴሩ ለምን ክትትልና ቁጥጥር ሳያደርግ ቀረ?

አቶ አምበሳው፡-በሥልጠና፣ በዕቅድ ዝግጅትና በውድድር ወቅት ቁጥጥርና ክትትል ለማድረግ ሞክረናል፡፡ ግን በቂ አልነበረም፡፡ በአጠቃላይ ግን ድጋፍ ማድረግም ኃላፊነታችን እንደሆነ እናውቃለን፡፡

ጥያቄ፡- የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ያለ ዋናው ጽሕፈት ቤት ኃላፊ እየተመራ እንዴት ወደ ስፍራው ሊያመራ ቻለ?

አቶ አምበሳው፡-የኦሊምፒክ ኮሚቴው ዋና ጸሐፊ በራሳቸው ፈቃድ ቦታውን ለቀዋል፡፡ ግን መተካት ነበረበት፤ ሳይተካ ቆይቷል፡፡ የኦሊምፒክ ኮሚቴው የሥራ ዘመኑን ስለጨረሰ፣ በቀጣይ ምርጫ ያካሂዳል፡፡ ከዚህ በኋላም በደንባቸው ላይ የጽሕፈት ቤት ኃላፊ ያስፈልጋል? አያስፈልግም የሚለውን ይወስናሉ፡፡ ምክንያቱም በተለያዩ አገሮች በጽሕፈት ቤት ኃላፊ የሚመሩ አሉ፡፡ የማይመሩም እንደዛው፡፡ ስለዚህም በቀጣይ የሚታይ ይሆናል፡፡

ጥያቄ፡- በመጨረሻም የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ያዘጋጀው ጋዜጣዊ መግለጫ ተገቢ አልነበረም የሚሉ አካላት ነበሩ፡፡ ምን ምላሽ ይሰጣሉ?

አቶ አምበሳው፡-ተገቢ አይደለም የተባለውን አልቀበልም፡፡ እንደእኛ ተገቢ ነው የሚል አቋም አለን፡፡

Standard (Image)

በኮፓ ኮካ ኮላ ታዳጊዎች የእግር ኳስ ውድድር 85 ተጫዋቾች ለአካዳሚ ተመረጡ

$
0
0

ከነሐሴ 21 እስከ 29 ቀን 2008 ዓ.ም. በቢሾፍቱ ከተማ ሲካሄድ የሰነበተው ከ15 ዓመት በታች የኮፓ ኮካ ኮላ እግር ኳስ ወድድር፣ ከሁለቱም ፆታ የተገኙ 85 ተጫዋቾችን በመምረጥ አዲስ አበባ ለሚገኘው የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ እንዲሁም አሰላ ከተማ ለሚገኘው የጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ ማበርከት አስችሏል፡፡

ለሁለተኛ ጊዜ የተካሄደው ውድድሩ ከሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የተመረጡ ታዳጊዎችን ያሳተፈ ሲሆን፣ ቀደም ብሎ 756 ወንድ፣ 744 ሴት ተወዳዳሪዎችን በመምረጥ በድምሩ 1,500 ታዳጊዎችን ሲያወዳድር ቆይቶ ነበር፡፡

በትምህርት ቤቶች በተደረገ ማጣሪያ ውድድርም 11 የወንድ ቡድኖችና 11 የሴት ቡድኖች ውድድራቸውን ሲያደርጉ ቆይተው ኦሮሚያ፣ ደቡብ፣ ቤኒሻንጉልና አማራ ክልሎች ለፍፃሜ መድረስ ችለዋል፡፡ ከኢትዮጵያ እግር ካስ ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር ለአሥር ቀናት ሲደረግ በቆየው የታዳጊ ወጣቶች የእግር ኳስ ውድድር፣ በተለይ ተተኪ ተጫዋቾችን ለማግኘት ትልቅ ዕድል የፈጠረ እንደሆነ የቀድሞ የብሔራዊ ቡድን ዋና አሠልጣኝ አቶ ሰውነት ቢሻው ተናግረዋል፡፡ አሠልጣኙ ‹‹ታዳጊዎቹ አካዳሚ ውስጥ ከገቡ በኋላ አስፈላጊው ክትትል እየተደረገላቸው ችሎታቸውን በማዳበር ለተለያዩ ክለቦችና ለብሔራዊ ቡድን የሚተርፍ አቅም ማሳየት ይችላሉ፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡ የ2008 ዓ.ም. የኮፓ ኮካ ኮላ ከ15 ዓመት በታች ውድድር እሑድ ነሐሴ 29 የተጠናቀቀ ሲሆን፣ በወንዶች ደቡብ፣ በሴቶች ኦሮሚያ የዋንጫ ባለቤት ሆነዋል፡፡

ኦሮሚያ ከደቡብ በተደረገው የሴቶች ጨዋታ ኦሮሚያ 3 ለ 1 በመለያ ምት አሸንፏል፡፡ በወንዶች ፍጻሜ ጨዋታ ደቡብ አማራን በመለያ ምት 4 ለ 2 ሲረታ፣ በአጠቃላይ በወንዶች አንደኛ ደቡብ 50 ሺሕ፣ አማራ 30 ሺሕ እንዲሁም ቤኒሻንጉል ጉሙዝ 20 ሺሕ ብር ተሸላሚ ሆነዋል፡፡ በሴቶች ኦሮሚያ፣ ደቡብና ቤኒሻንጉል እንደደረጃቸው ተመሳሳይ የገንዘብ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡

በ2007 ዓ.ም. የተዘጋጀው የኮፓ ኮካ ኮላ የታዳጊ ወጣቶች ውድድር አዳማ ላይ ሲካሄድ ለፍጻሜ ጨዋታው አፋርና ሶማሌ ክልሎች መድረሳቸው ይታወሳል፡፡ በዚህም መሠረት የመጨረሻው አራት ውስጥ መግባት የቻሉት እነዚህ ክልሎች ግን፣ የእግር ኳስ እንቅስቃሴ እምብዛም የማይስተዋልባቸው አካባቢዎች ናቸው፡፡ በመሆኑም በቀጣይ በአካባቢው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ትኩረት ሰጥቶ የበለጠ እንዲሠራ ፍንጭ የሰጠ እንደሆነ አቶ ታዬ ናኔቻ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ቴክኒክ ዲፓርትመንት የሕፃናትና ወጣቶች ዴስክ ተጠሪ በመዝጊያ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ገልጸዋል፡፡  

 

Standard (Image)
Viewing all 339 articles
Browse latest View live